ሆሴዕ 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሆሴዕ 3:1-5

የሆሴዕ ከሚስቱ ጋር መታረቅ

1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “እርሷ በሌላ ሰው የምትወደድ አመንዝራ ብትሆንም፣ አሁንም ሂድና ሚስትህን ውደዳት፤ ወደ ሌሎች አማልክት ዘወር ቢሉና ለእነርሱም የተቀደሰውን የዘቢብ ጥፍጥፍ ቢወድዱም፣ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንደ ወደዳቸው አንተም እርሷን ውደዳት።”

2ስለዚህ በዐሥራ አምስት ሰቅል ጥሬ ብርና በአንድ ቆሮስ ተኩል መስፈሪያ ገብስ ገዛኋት። 3እኔም፣ “ከእኔ ጋር ብዙ ቀን ተቀመጪ፤3፥3 ወይም ቈዪ አታመንዝሪ ወይም ሌላ ሰው አትውደጂ፤ እኔም ከአንቺ ጋር እኖራለሁ” ብዬ ነገርኋት።

4እስራኤላውያን ለብዙ ዘመን ያለ ንጉሥና ያለ አለቃ፣ ያለ መሥዋዕትና ያለ ዐምደ ጣዖት፣ ያለ ኤፉድና ያለ ጣዖት ምስል ይኖራሉና። 5ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በመጨረሻውም ዘመን በመንቀጥቀጥ ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።