ገላትያ 4 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ገላትያ 4:1-31

1እኔ የምለው ይህ ነው፤ ወራሹ ሕፃን እስከ ሆነ ድረስ፣ ሀብት ሁሉ የእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ከባሪያ የተለየ አይደለም። 2አባቱ እስከ ወሰነለት ጊዜ ድረስ በጠባቂዎችና በሞግዚቶች ሥር ነው። 3እኛም እንዲሁ ገና ልጆች በነበርንበት ጊዜ፣ ከዓለም መሠረታዊ ትምህርት ሥር በመሆን በባርነት ተገዝተን ነበር። 4ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ 5ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው። 6ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር፣ “አባ፣4፥6 በአረማይኩ አባት ማለት ነው። አባት” ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን ላከ።

7ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ስለ ሆንህ፣ እግዚአብሔር ወራሽ አድርጎሃል።

ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ማሰቡ

8እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ 9አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በእርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን? 10ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ። 11ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።

12ወንድሞች ሆይ፤ እለምናችኋለሁ፤ እኔ እናንተን እንደ መሰልሁ፣ እናንተም እኔን ምሰሉ። እናንተ አንዳች አልበደላችሁኝም። 13እንደምታውቁት፣ በመጀመሪያ ለእናንተ ወንጌልን የሰበክሁት በሕመም ምክንያት ነበር። 14ሕመሜ ለእናንተ ፈተና ሆኖባችሁም እንኳ፣ አልሰለቻችሁኝም፤ ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንዲያውም እንደ ራሱ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ። 15ለመሆኑ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ደረሰ? ቢቻላችሁ ዐይናችሁን ቢሆን እንኳ አውጥታችሁ የምትሰጡኝ እንደ ነበራችሁ እመሰክራለሁ። 16እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?

17እነዚያ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሊወስዷችሁ ይተጋሉ፤ ለበጎ ግን አይደለም፤ የሚፈልጉት እናንተን ከእኛ ነጥለው የራሳቸው ሊያደርጓችሁ ነው። 18ለበጎ እስከ ሆነ ድረስ ተቈርቋሪ መሆን መልካም ነው፤ ይህም መሆን የሚገባው ዘወትር እንጂ እኔ ከእናንተ ጋር ሳለሁ ብቻ አይደለም። 19የምወድዳችሁ ልጆቼ ሆይ፤ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ፣ ስለ እናንተ እንደ ገና ምጥ ይዞኛል፤ 20ስለ እናንተ ግራ በመጋባት ተጨንቄአለሁና፤ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ ቋንቋ ልናገራችሁ ምን ያህል በወደድሁ!

አጋርና ሣራ ምሳሌ መሆናቸው

21እናንት ከኦሪት ሕግ በታች ለመኖር የምትሹ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕግ ምን እንደሚል አልሰማችሁምን? 22አብርሃም፣ አንዱ ከባሪያዪቱ፣ ሌላው ደግሞ ከነጻዪቱ ሴት የሆኑ ሁለት ልጆች እንደ ነበሩት ተጽፏልና። 23ባሪያ ከነበረችው ሴት የተገኘው ልጅ እንደ ሥጋ ልማድ ነበር፤ ከነጻዪቱ ሴት የተወለደው ግን በተስፋው ቃል መሠረት ነው።

24እነዚህ ሴቶች ሁለቱን ኪዳኖች ስለሚያመለክቱ፣ ይህ ሁኔታ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። አንደኛዋ ኪዳን ከሲና ተራራ ስትሆን፣ ለባርነት የሚሆኑ ልጆችን የምትወልድ ናት፤ እርሷም አጋር ናት። 25እንግዲህ አጋር በዐረብ አገር ያለችው የሲናን ተራራ በመወከል አሁን ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፤ ከልጇ ጋር በባርነት ናትና። 26ከላይ የሆነችው ኢየሩሳሌም ግን በነጻነት ትኖራለች፤ እርሷም እናታችን ናት። 27እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤

ደስ ይበልሽ፤

አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣

በእልልታ ጩኺ፤

ባል ካላት ይልቅ፣

የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”

28እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ። 29በዚያን ጊዜ እንደ ሥጋ ልማድ የተወለደው ልጅ፣ በመንፈስ ኀይል የተወለደውን አሳደደው፤ አሁንም እንደዚያው ነው። 30ነገር ግን መጽሐፍ ምን ይላል? “ባሪያዪቱን ከልጇ ጋር አስወግዳት፤ የባሪያዪቱ ልጅ ከነጻዪቱ ልጅ ጋር አይወርስምና” ይላል። 31ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ እኛ የነጻዪቱ እንጂ የባሪያዪቱ ልጆች አይደለንም።