ዳንኤል 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዳንኤል 11:1-45

1እኔም፣ ሜዶናዊው ዳርዮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣ እርሱን ለማገዝና ለማበረታታት በአጠገቡ ቆሜ ነበር።

የሰሜንና የደቡብ ነገሥታት

2“አሁንም እውነቱን እነግርሃለሁ፤ እነሆ፤ ሦስት ሌሎች ነገሥታት በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል። በባለጠግነቱም እጅግ በበረታ ጊዜ፣ ሌላውን ሁሉ አሳድሞ በግሪክ መንግሥት ላይ ያስነሣል። 3ከዚያም በታላቅ ኀይል የሚገዛና የወደደውንም ሁሉ የሚያደርግ ኀያል ንጉሥ ይነሣል። 4በኀይል እየገነነ ሳለም፣ መንግሥቱ ይፈርሳል፤ ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳትም ይከፋፈላል። መንግሥቱ ተወስዶ ለሌሎች ስለሚሰጥ፣ ለዘሩ አይተላለፍም፤ ኀይሉም እንደ መጀመሪያው አይሆንም።

5“የደቡቡ ንጉሥ ይበረታል፤ ነገር ግን ከጦር አዛዦቹ አንዱ ከእርሱ የበለጠ የበረታ ይሆናል፤ ግዛቱም ታላቅ ይሆናል። 6ከጥቂት ዓመታት በኋላም አንድነት ይፈጥራሉ። የደቡቡ ንጉሥ ሴት ልጅ ስምምነት ለማድረግ ወደ ሰሜኑ ንጉሥ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ኀይሏን ይዛ መቈየት አትችልም፤ እርሱም ሆነ የእርሱ ኀይል11፥6 ወይም ዘሩ አይጸናም። በእነዚያ ቀናት እርሷ ከቤተ መንግሥት አጃቢዎቿ፣ ከአባቷና11፥6 ወይም ከልጇና (ቫልጌትንና ሱርስትን ይመ) ከደጋፊዎቿ ጋር ዐልፋ ትሰጣለች።

7“ከዘመዶቿ አንዱ ስፍራዋን ሊይዝ ይነሣል፤ የሰሜንን ንጉሥ ሰራዊት ይወጋል፤ ምሽጎቹንም ጥሶ ይገባል፤ ከእነርሱም ጋር ተዋግቶ ድል ያደርጋል። 8አማልክታቸውን፣ የብረት ምስሎቻቸውን፣ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ የከበሩ ዕቃዎቻቸውን ይማርካል፤ ወደ ግብፅም ይወስዳል። ለጥቂት ዓመታትም ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር ከመዋጋት ይቈጠባል። 9የሰሜኑም ንጉሥ፣ የደቡቡን ንጉሥ ግዛት ይወርራል፤ ነገር ግን አፈግፍጎ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል። 10ወንዶች ልጆቹም ለጦርነት ይዘጋጃሉ፤ እስከ ጠላት ምሽግ ደርሶ የሚዋጋና ሊቋቋሙት እንደማይቻል ጐርፍ የሚጠራርግ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባሉ።

11“ከዚያም የደቡቡ ንጉሥ በቍጣ ወጥቶ የሰሜኑን ንጉሥ ይወጋል። የሰሜኑ ንጉሥ ታላቅ ሰራዊት ቢያሰባስብም ይሸነፋል። 12የደቡቡ ንጉሥ ብዙ ሰራዊት በሚማርክበት ጊዜ ልቡ በትዕቢት ይሞላል፤ በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ ሰዎችንም ይገድላል፤ ነገር ግን በድል አድራጊነቱ አይጸናም። 13የሰሜን ንጉሥ ከመጀመሪያው የሚበልጥ ታላቅ ሰራዊት ያሰባስባል፤ ከብዙ ዓመትም በኋላ በትጥቅ እጅግ ከተደራጀ ታላቅ ሰራዊት ጋር ተመልሶ ይመጣል።

14“በዚያም ዘመን ብዙዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ራእዩ ይፈጸም ዘንድ፣ ከሕዝብህ መካከል ዐመፀኛ የሆኑ ሰዎች ይነሣሉ፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም። 15የሰሜኑም ንጉሥ መጥቶ የዐፈር ድልድል ይክባል፤ የተመሸገችውንም ከተማ ይይዛል። የደቡቡ ሰራዊትም ለመቋቋም ኀይል ያጣል፤ የተመረጡት ተዋጊዎቻቸው እንኳ ጸንተው መዋጋት አይችሉም። 16ወራሪው ደስ ያሰኘውን ያደርጋል፤ ማንም ሊቋቋመው አይችልም። በመልካሚቱ ምድር ላይ ይገዛል፤ እርሷን ለማጥፋትም ኀይል ይኖረዋል። 17በመንግሥቱ ያለውን ሰራዊት ሁሉ ይዞ ለመምጣት ይወስናል፤ ከደቡብም ንጉሥ ጋር ይስማማል፤ ይህንም መንግሥት ለመጣል ሴት ልጁን ይድርለታል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ11፥17 ወይም እርሷ አይሳካለትም፤ ያሰበውም ነገር አይጠቅመውም። 18ከዚህም በኋላ በባሕር ጠረፍ ወዳሉት አገሮች ፊቱን በመመለስ ብዙዎቹን ይይዛል፤ ነገር ግን አንድ አዛዥ ትዕቢቱን ያከሽፍበታል፤ በራሱም ላይ ይመልስበታል። 19በገዛ አገሩ ወዳሉት ምሽጎችም ፊቱን ይመልሳል፤ ነገር ግን ተሰናክሎ ይወድቃል፤ ዳግምም አይታይም።

20“በእርሱ ቦታ የሚተካውም የመንግሥቱን ክብር ለማስጠበቅ ግብር አስገባሪ ይልካል፤ ይሁን እንጂ በቍጣ ወይም በጦርነት ሳይሆን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይገደላል።

21“በእርሱም ፈንታ የተናቀ ሰው ይነግሣል፤ ንጉሣዊ ክብርም አይሰጠውም፤ ሕዝቡ በሰላም ተቀምጦ ሳለ በተንኰል መንግሥቱን ይይዛል። 22ከፊቱ የሚቆመውን ታላቅ ሰራዊት፣ የቃል ኪዳኑንም አለቃ ሳይቀር ይደመስሳል። 23ከእርሱ ጋር ስምምነት ከተደረገ በኋላ የማታለል ሥራውን ይሠራል፤ ከጥቂት ሰዎች ጋር ለሥልጣን ይበቃል። 24የበለጸጉትን ክፍለ አገሮች በሰላም ሳሉ በድንገት ይወርራቸዋል፤ አባቶቹም ሆኑ አያቶቹ ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል፤ ይከናወንለታልም፤ ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና የተገኘውን ሀብት ሁሉ ለተከታዮቹ ያካፍላቸዋል፤ ምሽጎችን ለመጣል ያሤራል፤ ይህን የሚያደርገውም ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።

25“ታላቅ ሰራዊት አደራጅቶ ኀይሉንና ብርታቱን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያነሣሣል፤ የደቡብ ንጉሥም ቍጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኀያል ሰራዊት ይዞ ጦርነትን ያውጃል፤ ነገር ግን ከተዶለተበት ሤራ የተነሣ መቋቋም አይችልም። 26ከንጉሥ ማዕድ አብረውት ሲበሉ የነበሩት ሊያጠፉት ያሤራሉ፤ ሰራዊቱም ይደመሰሳል፤ ብዙዎቹም በጦርነት ይወድቃሉ። 27ልባቸው ወደ ክፋት ያዘነበለው ሁለቱ ነገሥታት፣ በአንድ ገበታ አብረው ይቀመጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ሐሰትን ይነጋገራሉ፤ ነገር ግን የተወሰነው ጊዜ ገና ስለሆነ አይከናወንላቸውም። 28የሰሜን ንጉሥ ብዙ ሀብት ይዞ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል፤ ነገር ግን ልቡ በተቀደሰው ኪዳን ላይ ይነሣሣል፤ ክፉ ነገርም ያደርግበታል፤ ከዚያም ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

29“በተወሰነው ጊዜ ደቡቡን እንደ ገና ይወርራል፤ በዚህ ጊዜ ግን ውጤቱ ከበፊቱ የተለየ ይሆናል። 30የኪቲም11፥30 ወይም የምዕራብ ባሕር ዳር አገሮች መርከቦች ይቃወሙታል፤ ልቡም ይሸበራል። ወደ ኋላም ይመለሳል፤ ቍጣውን በተቀደሰው ኪዳን ላይ ያወርዳል፤ ተመልሶም የተቀደሰውን ኪዳን የተዉትን ይንከባከባል።

31“የጦር ሰራዊቶቹም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሩን ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ በዚያም ጥፋትን የሚያመጣውን የጥፋት ርኩሰት ይተክላሉ። 32ኪዳኑን የሚተላለፉትን በማታለል ያስታል፤ አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ጸንተው ይቃወሙታል፤ ርምጃም ይወስዳሉ።

33“ለጊዜው በሰይፍ ቢወድቁም፣ ቢቃጠሉም፣ ቢማረኩና ቢዘረፉም፣ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ብዙዎችን ያስተምራሉ። 34በሚወድቁበት ጊዜ መጠነኛ ርዳታ ያገኛሉ፤ እውነተኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎችም ይተባበሯቸዋል። 35ጥበበኛ ከሆኑ ሰዎች አንዳንዶቹ ይሰናከላሉ፤ ይህም እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የጠሩ፣ የነጠሩና እንከን የሌለባቸው ይሆኑ ዘንድ ነው፤ የተወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰምና።

ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ንጉሥ

36“ንጉሡ ደስ እንዳለው ያደርጋል፤ ከአማልክት ሁሉ በላይ ራሱን እጅግ ከፍ በማድረግ በአማልክት አምላክ ላይ ተሰምቶ የማይታወቅ የስድብ ቃል ይናገራል፤ የቍጣውም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ይሳካለታል፤ የተወሰነው ነገር ሁሉ መሆን አለበትና። 37ሴቶች ለሚወድዱትም ሆነ ለአባቶቹ አማልክት ክብርን አይሰጥም፤ ማንኛውንም አምላክ አያከብርም፤ ነገር ግን ራሱን ከእነዚህ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል። 38በእነርሱም ምትክ የምሽጎችን አምላክ ያከብራል፤ አባቶች የማያውቁትን አምላክ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮችና በውድ ስጦታዎች ያከብራል። 39በባዕድ አምላክ ርዳታ ጽኑ ምሽጎችን ይወጋል፤ ለእርሱ የሚገዙትን በእጅጉ ያከብራቸዋል፤ በብዙ ሕዝብ ላይ ገዦች ያደርጋቸዋል፤ ምድሩንም በዋጋ ያከፋፍላቸዋል።

40“በመጨረሻው ዘመን የደቡብ ንጉሥ ጦርነት ያውጅበታል፤ የሰሜን ንጉሥም በፈረሰኞችና በሠረገሎች፣ በብዙ መርከቦችም እንደ ማዕበል ይመጣበታል፤ ብዙ አገሮችን ይወርራል፤ እንደ ጐርፍም እየጠራረገ በመካከላቸው ያልፋል። 41መልካሚቱንም ምድር ይወርራል፤ ብዙ አገሮች በእጁ ይወድቃሉ፤ ኤዶም፣ ሞዓብና የአሞን መሪዎች ግን ከእጁ ያመልጣሉ። 42ሥልጣኑን በብዙ አገሮች ላይ ያንሰራፋል፤ ግብፅም አታመልጥም። 43የወርቅና የብር ክምችትን፣ እንዲሁም የግብፅን ሀብት ሁሉ በቍጥጥሩ ሥር ያደርጋል፤ የሊቢያና የኢትዮጵያ11፥43 ወይም የኑብያ ወይም የኵሽ ሰዎችም ይገዙለታል። 44ነገር ግን ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣ ወሬ ያስደነግጠዋል፤ ብዙዎችንም ለማጥፋትና ለመደምሰስ በታላቅ ቍጣ ይወጣል። 45ንጉሣዊ ድንኳኖቹን በባሕሮች መካከል11፥45 ወይም በባሕርና ውብ…መካከል ውብ በሆነው ቅዱስ ተራራ ላይ ይተክላል፤ ይሁን እንጂ ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ ማንም አይረዳውም።”