ዮሐንስ 17 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዮሐንስ 17:1-26

ኢየሱስ ስለ ራሱ መጸለዩ

1ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤

“አባት ሆይ፤ ጊዜው ደርሷል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ 2ከአንተ ለተቀበላቸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲሰጥ፣ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥተኸዋልና። 3እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። 4የሰጠኸኝን ሥራ በመፈጸም በምድር አከበርሁህ። 5እንግዲህ አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ።

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ጸለየ

6“ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። የአንተ ነበሩ ለእኔ ሰጠኸኝ፤ እነርሱም ቃልህን ጠብቀዋል። 7የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ዐውቀዋል፤ 8ምክንያቱም የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸው ተቀብለዋል፤ እኔም ከአንተ እንደ ወጣሁ በርግጥ ዐውቀዋል፤ አንተ እንደ ላክኸኝም አምነዋል፤ 9እነርሱ የአንተ ስለሆኑ እጸልይላቸዋለሁ፤ ለሰጠኸኝና የአንተ ለሆኑት እንጂ ለዓለም አልጸልይም። 10የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነውም ሁሉ የእኔ ነው፤ በእነርሱም ከብሬአለሁ። 11ከእንግዲህ እኔ በዓለም አልቈይም፤ እነርሱ ግን በዓለም ውስጥ ናቸው፤ እኔም ወደ አንተ መምጣቴ ነው። ቅዱስ አባት ሆይ፤ እኛ አንድ እንደ ሆንን፣ እነርሱም አንድ እንዲሆኑ በሰጠኸኝ በስምህ ጠብቃቸው። 12እኔ ከእነርሱ ጋር ሳለሁ፣ በሰጠኸኝ ስም ከለልኋቸው፤ ጠበቅኋቸውም፤ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ከአንዱ ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም።

13“አሁን ወደ አንተ መምጣቴ ነው፤ ነገር ግን ደስታዬ በእነርሱ ዘንድ የተሟላ እንዲሆን፣ አሁን በዓለም እያለሁ ይህን እናገራለሁ። 14ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ፣ እነርሱም ከዓለም ባለመሆናቸው ዓለም ጠልቷቸዋል። 15የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። 16እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም። 17ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው17፥17 በግሪኩ ሀጊያዞ የሚለው ቅዱስ ለሆነ ተግባር መለየት ወይም መቀደስ ማለት ነው፤ 19 ይመ 18አንተ ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እኔም ወደ ዓለም ልኬአቸዋለሁ። 19እነርሱ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሻለሁ።”

ኢየሱስ ለአማኞች ሁሉ ጸለየ

20“የእነርሱን ትምህርት ተቀብለው በእኔ ለሚያምኑ ጭምር እንጂ ለእነዚህ ብቻ አልጸልይም፤ 21ይህም፣ አባት ሆይ፤ አንተ በእኔ፣ እኔም በአንተ እንዳለሁ ሁሉም አንድ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም አንተ እኔን እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፣ እነርሱም በእኛ እንዲሆኑ ነው። 22እኛ አንድ እንደ ሆንን እነርሱም አንድ እንዲሆኑ፣ የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለሁ። 23ይህም እኔ በእነርሱ፣ አንተም በእኔ መሆንህ ነው። አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድኸኝ መጠን እነርሱንም እንደ ወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ፣ አንድነታቸው ፍጹም ይሁን።

24“አባት ሆይ፤ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እንዲሆኑ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝንም ክብሬን እንዲያዩ እፈልጋለሁ።

25“ጻድቅ አባት ሆይ፤ ዓለም ባያውቅህም፣ እኔ ዐውቅሃለሁ፤ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ ያውቃሉ። 26ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ17፥26 በግሪኩ ስምህን እንዲያወቁ ይላል። አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ።”