1የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤
ለተጠሩት፣ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት1፥1 ወይም የተጠበቁት ሊሆን ይችላል፤
2ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ።
የዐመፀኞች ኀጢአትና የሚጠብቃቸው ፍርድ
3ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጕቼ ነበር፤ ነገር ግን ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። 4ከረዥም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ1፥4 ወይም ፍርድ የተወሰነባቸውን ሰዎች የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኩሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።
5ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ይህን ሁሉ የምታውቁ ቢሆንም፣ ጌታ1፥5 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ኢየሱስ ይላሉ። ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ፣ በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወድዳለሁ። 6የሥልጣን ስፍራቸውን ያልጠበቁትን፣ ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቋቸዋል። 7እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ፣ በዙሪያቸውም ያሉ ከተሞች ለሴሰኝነትና ከተፈጥሮ ሥርዐት ውጭ ለሆነ ሩካቤ ሥጋ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት በመቀጣት ለሚሠቃዩት ምሳሌ ሆነዋል።
8በዚህ ሁኔታ እነዚህ ሕልም ዐላሚዎች የገዛ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ሥልጣንን ይቃወማሉ፤ በሰማይ ክብር ያላቸውንም ፍጥረታት ይሳደባሉ። 9የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል እንኳ ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ፣ “ጌታ ይገሥጽህ” አለው እንጂ የስድብ ቃል በመናገር ሊከስሰው አልደፈረም። 10እነዚህ ሰዎች ግን የማያውቁትን ነገር ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት በደመ ነፍስ በሚያወቁት ነገር ይጠፋሉ።
11ወዮላቸው! በቃየን መንገድ ሄደዋል፤ ለገንዘብ ሲስገበገቡ በበለዓም ስሕተት ውስጥ ወድቀዋል፤ በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋል።
12እነዚህ ሰዎች በፍቅር ግብዣችሁ ላይ ያለ አንዳች ኀፍረት ከእናንተ ጋር ቀርበው የሚበሉ ነውረኞች ናቸው፤ ደግሞም ራሳቸውን ብቻ የሚመግቡ እረኞች ናቸው፤ እነርሱም በነፋስ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ናቸው፤ በመከር ወራት ፍሬ የማይገኝባቸው ከሥራቸው ተነቅለው ሁለት ጊዜ የሞቱ ዛፎች ናቸው። 13የነውራቸውን ዐረፋ የሚደፍቁ የተቈጡ የባሕር ማዕበል፣ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የሚጠብቃቸው ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።
14ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ተንብዮአል፤ “እነሆ፤ ጌታ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል፤ 15ይህም፣ በሰው ሁሉ ላይ ለመፍረድ እንዲሁም ዐመፀኞችን ሁሉ በክፋት መንገድ በሠሩት የዐመፅ ሥራና በክፋት በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩት የስድብ ቃል ሁሉ አጥፊነታቸውን ይፋ ለማድረግ ነው።” 16እነዚህ ሰዎች የሚያጕረመርሙና ሌሎችን ሰዎች የሚከስሱ ናቸው፤ ርኩስ ምኞታቸውን ይከተላሉ፤ በራሳቸው ይታበያሉ፤ ጥቅም ለማግኘት ሲሉም ሌሎችን ይክባሉ።
ጸንቶ ስለ መቆም የቀረበ ጥሪ
17ነገር ግን ወዳጆች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን አስታውሱ። 18እነርሱም፣ “በመጨረሻው ዘመን ርኩስ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ” ብለዋችኋል። 19እነዚህ ሰዎች በመካከላችሁ መለያየትን የሚፈጥሩ፣ በደመ ነፍስ የሚነዱና መንፈስ የሌላቸው ናቸው።
20እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ። 21ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
22ተጠራጣሪ ለሆኑት ራሩላቸው፤ 23አንዳንዶችን ከእሳት ነጥቃችሁ አድኗቸው፤ ለሌሎች ደግሞ በርኩስ ሥጋ የተበከለውን ልብሳቸውን እንኳ እየጠላችሁ በፍርሀት ምሕረት አሳዩአቸው።
ቃለ ውዳሴ
24እንዳትወድቁ ሊጠብቃችሁና ያለ ነቀፋና በደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው፣ 25እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለምም ድረስ ክብር፣ ግርማ፣ ኀይልና ሥልጣን ይሁን፤ አሜን።