ዘዳግም 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 8:1-20

እግዚአብሔርን አትርሳ

1በሕይወት እንድትኖሩ፣ እንድትበዙና እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ በመሐላ ተስፋ የገባላቸውን ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፣ ዛሬ እኔ የምሰጥህን እያንዳንዱን ትእዛዝ ለመከተል ጥንቃቄ አድርጉ። 2አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞቹን መጠበቅህንና በልብህ ያለውን ለማወቅ፣ ትሑት ሊያደርግህና ሊፈትንህ በእነዚህ አርባ ዓመታት በዚህ ምድረ በዳ ጕዞህ ሁሉ እንዴት እንደ መራህ አስታውስ። 3ሰው ከእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤ 4በእነዚህ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብስህ አላለቀም፤ እግርህም አላበጠም። 5ስለዚህ ሰው ልጁን እንደሚቀጣ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም ያህዌ) አንተን እንደሚቀጣህ በልብህ ዕወቅ።

6በመንገዶቹ በመሄድና እርሱንም በማክበር፣ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ጠብቅ። 7አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ጅረቶችና የኵሬ ውሃ ወዳለበት፣ ምንጮች ከየሸለቆውና ከየኰረብታው ወደሚፈስሱበት ወደ መልካሚቱ ምድር ያገባሃል፣ 8ስንዴና ገብስ፣ ወይንና የበለስ ዛፎች፣ ሮማን፣ የወይራ ዘይትና ማር የሚገኝባት ምድር፤ 9ምንም ነገር የማይታጣባት፣ የዳቦም ዕጦት የሌለባት፣ ዐለቶች ብረት የሆኑባት፣ ከኰረብቶቿም መዳብ ቈፍረህ ልታወጣ የምትችልባት ምድር ናት።

10በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ እንዲህ ያለች መልካም ምድር ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ባርከው። 11በዛሬዪቱ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንዳትረሳው ተጠንቀቅ። 12አለዚያ በልተህ ስትጠግብና ጥሩ ጥሩ ቤቶችን ሠርተህ መኖር ስትጀምር፣ 13ደግሞም የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህ ሲበዛ፣ ብርህና ወርቅህ ሲበረክት፣ ያለህም ሁሉ በላይ በላዩ እየጨመረ ሲሄድ፣ 14ልብህ ይታበይና ከባርነት ምድር፣ ከግብፅ ያወጣህን አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትረሳለህ። 15በዚያ ጭልጥ ባለና አስፈሪ ምድረ በዳ፣ በዚያ በሚያስጠማና ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት፣ መርዘኛ እባብና ጊንጥ ባለበት ምድረ በዳ መራህ፤ ከጽኑ ዐለትም ውሃ አፈለቀልህ። 16በመጨረሻ መልካም እንዲሆንልህ፣ አንተን ትሑት ለማድረግና ለመፈተን፣ አባቶችህ ፈጽሞ የማያውቁትን መና በምድረ በዳ መገበህ። 17ምናልባትም፣ “ይህን ሀብት ያፈራሁት በጕልበቴና በእጄ ብርታት ነው” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል። 18ነገር ግን ሀብት እንድታፈራ ችሎታ የሰጠህ፣ ለአባቶችህም በመሐላ የገባውን ኪዳን ያጸናልህ እርሱ ስለሆነ፣ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ዐስበው።

19አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትረሳና ሌሎችን አማልክት ብትከተል፣ ብታመልክና ለእነርሱ ብትሰግድላቸው በርግጥ እንደምትጠፉ ዛሬ እመሰክርባችኋለሁ። 20እግዚአብሔር (ያህዌ) ከፊታችሁ ያሉትን አሕዛብ እንዳጠፋቸው ሁሉ፣ ለአምላካችሁ ለአግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባለመታዘዛችሁ እናንተም ትጠፋላችሁ።