ዘዳግም 28 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 28:1-68

በመታዘዝ የሚገኝ በረከት

1ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል። 2አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም።

3በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ።

4የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ።

5እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ ይባረካሉ።

6ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ።

7እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ።

8እግዚአብሔር (ያህዌ) በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል።

9የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤ 10ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። 11እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።

12እግዚአብሔር (ያህዌ) ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም። 13እግዚአብሔርም (ያህዌ) ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፣ መቼውንም ቢሆን በላይ እንጂ ፈጽሞ በታች አትሆንም። 14ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።

አለመታዘዝ የሚያስከትላቸው ርግማኖች

15ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦

16በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።

17እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ የተረገሙ ይሆናሉ።

18የማሕፀንህ ፍሬ፣ የዕርሻህ ሰብል፣ የመንጋህ ጥጆች፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህ ይረገማሉ።

19ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ።

20እርሱን28፥20 ዕብራይስጡ፣ እኔን ይላል። በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፣ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ርግማንን፣ መደናገርንና ተግሣጽን ይሰድድብሃል። 21እግዚአብሔር (ያህዌ) ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪያጠፋህ ድረስ በደዌ ይቀሥፍሃል። 22እግዚአብሔር (ያህዌ) እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ ደዌ፣ ትኵሳትና ዕባጭ፣ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፣ ዋግና አረማሞ ይመታሃል። 23ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ ናስ፣ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም ብረት ይሆናል። 24እግዚአብሔር (ያህዌ) የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።

25እግዚአብሔር (ያህዌ) በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መሸማቀቂያ ትሆናለህ። 26ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ በማስፈራራትም የሚያባርራቸው አይኖርም። 27እግዚአብሔር (ያህዌ) በማትድንበት በግብፅ ብጉንጅ፣ በዕባጭ፣ በሚመግል ቍስልና በዕከክ ያሠቃይሃል። 28እግዚአብሔር (ያህዌ) በእብደት፣ በዕውርነትና ግራ በማጋባት ያስጨንቅሃል። 29በእኩለ ቀን፣ በጨለማ እንዳለ ዕውር በዳበሳ ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። በየዕለቱ ትጨቈናለህ፤ ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም።

30ሚስት ለማግባት ልጃገረድ ታጫለህ፤ ሌላው ግን ወስዶ ይደፍራታል። ቤት ትሠራለህ፣ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም። 31በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም። 32ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ በማለትም ዐይኖችህ ሁልጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ። 33የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በጭቈና ከመኖር በቀር የሚተርፍህ ነገር አይኖርም። 34የምታየው ሁሉ ያሳብድሃል። 35እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጕር በሚዛመት፣ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቍስል ጕልበትህንና እግርህን ይመታሃል።

36እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 37እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ መሸማቀቂያ፣ ማላገጫና መዘባበቻ ትሆናለህ።

38በዕርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው ግን፣ የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል። 39ወይን ትተክላለህ፤ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ዘለላውን አትሰበስብም። 40በአገርህ ምድር ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን፣ ዘይቱን አትጠቀምበትም። 41ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ አብረውህ አይኖሩም። 42ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይወርረዋል።

43በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል፣ አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።

45እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፤ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስላልታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዐት ስላልጠበቅህ እስክትጠፋ ድረስ ይከተሉሃል፤ ይወርዱብሃልም። 46ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም ምልክትና መገረም ይሆናሉ። 47በብልጽግና ጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በደስታና በሐሤት ስላላገለገልኸው፣ 48በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል።

49እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋውን የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፣ ከምድርም ዳርቻ ያስነሣብሃል፤ 50ሽማግሌ የማያከብር፣ ለብላቴና የማይራራ፣ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው። 51እስክትጠፋም ድረስ የእንስሳትህን ግልገልና የምድርህን ሰብል ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነ ዘይት፣ የመንጋህን ጥጃ ሆነ የበግና ፍየል መንጋህን ግልገል አያስቀርልህም። 52የምትታመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪወድቁ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከብባል፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወርራቸዋል።

53ጠላቶችህ ከብበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጠህን፣ የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54ሌላው ይቅርና በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ ወይም ለሚወድዳት ሚስቱ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይራራላቸውም። 55ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታህል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ከተሞችህ ሁሉ በመከበባቸው ጠላቶችህ ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ለእርሱ የቀረለት ይህ ብቻ ነውና። 56በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ፣ እግሯን ዐፈር ነክቶት የማያውቅ ሴት፣ የምትወድደውን ባሏን፣ የገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆቿን ትንቃለች። 57ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጇንና የምትወልዳቸውን ሕፃናት ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከብበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ እነርሱን ደብቃ ለመብላት ስትል ነው።

58በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም ባታከብር፣ 59እግዚአብሔር (ያህዌ) አስፈሪ መቅሠፍት፣ አስጨናቂና ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መዓት፣ አሠቃቂና በቀላሉ የማይወገድ ደዌ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል። 60የምትፈራቸውንም የግብፅ በሽታዎች ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ። 61ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም ዐይነት ደዌና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል። 62ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስላልታዘዛችሁ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ። 63እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በማበልጸግና ቍጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሰኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።

64ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ። 65በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ ቦታ አይኖርም። እዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚጨነቅ አእምሮ፣ በናፍቆት የሚደክም ዐይንና ተስፋ የሚቈርጥ ልብ ይሰጥሃል። 66ቀንም ሆነ ሌሊት በፍርሀት እንደ ተዋጥህ፣ ሕይወትህ ዋስትና ሳታገኝ፣ ዘወትር በሥጋት ትኖራለህ። 67ልብህ በፍርሀት ከመሞላቱና ዐይንህ ከሚያየው የተነሣ፣ ሲነጋ፣ “ምነው አሁን በመሸ!” ሲመሽ ደግሞ፣ “ምነው አሁን በነጋ!” ትላለህ። 68ዳግመኛ አትመለስባትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር (ያህዌ) በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል። እዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሮች እንድትሆኗቸው ለጠላቶቻችሁ ለመሸጥ ራሳችሁን ታቀርባላችሁ፤ የሚገዛችሁ ግን አይኖርም።