ዘካርያስ 9 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘካርያስ 9:1-17

በእስራኤል ጠላቶች ላይ የተወሰነ ፍርድ

1የእግዚአብሔር ቃል ንግር በሴድራክ ምድር ላይ ይወርድበታል፤

በደማስቆም ላይ ያርፍበታል፤

የሰዎችና የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ዐይን፣

በእግዚአብሔር ላይ9፥1 ወይም ደማስቆ የእግዚአብሔር ዐይን በሰው ሁሉ ላይ ያያልና በእስራኤል ነገዶች ላይ እንደ ሆነው። ዐርፏልና።

2ደግሞም በአዋሳኟ በሐማት፣

ጥበበኞች ቢሆኑም እንኳ በጢሮስና በሲዶና ላይ ያርፍባቸዋል።

3ጢሮስ ለራሷ ምሽግ ሠርታለች፤

ብሩን እንደ ዐፈር

ወርቁንም እንደ መንገድ ላይ ትቢያ ቈልላለች።

4ጌታ ግን ሀብቷን ይወስዳል፤

በባሕር ያላትንም ኀይል ይደምስሳል፤

እርሷም በእሳት ፈጽማ ትጠፋለች።

5አስቀሎና አይታ ትርዳለች፤

ጋዛ በሥቃይ ትቃትታለች፤

አቃሮናም እንደዚሁ ትሠቃያለች፤ ተስፋዋ ይመነምናልና።

ጋዛ ንጉሥዋን ታጣለች፤

አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች።

6ድብልቅ ሕዝቦች አዛጦንን ይይዛሉ፤

የፍልስጥኤማውያንንም ትምክሕት እቈርጣለሁ።

7ደሙን ከአፋቸው፣

የተከለከለውንም ምግብ ከመንጋጋቸው አወጣለሁ።

የተረፉት ለአምላካችን ይሆናሉ፤

በይሁዳም አለቆች ይሆናሉ፤

አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።

8እኔ ግን ቤቴን

ከዘራፊ ኀይሎች እጠብቃለሁ፤

ጨቋኝ ከእንግዲህ ሕዝቤን አይወርስም፤

አሁን ነቅቼ እጠብቃለሁና።

የጽዮን ንጉሥ መምጣት

9አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤

አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤

እነሆ፤ ጻድቁና አዳኙ ንጉሥሽ9፥9 ወይም ንጉሥ ማለት ይሆናል

ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣

በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ

ወደ አንቺ ይመጣል።

10ሠረገሎችን ከኤፍሬም፣

የጦር ፈረሶችን ከኢየሩሳሌም እወስዳለሁ፤

የጦርነቱም ቀስት ይሰበራል፤

ሰላምን ለአሕዛብ ያውጃል፤

ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣

ከወንዙም9፥10 ኤፍራጥስም ነው እስከ ምድር9፥10 ወይም፣ ምድር ዳርቻ ማለት ነው። ዳር ድረስ ይዘረጋል።

11ለአንቺ ደግሞ፣ ከአንቺ ጋር ከገባሁት የደም ቃል ኪዳን የተነሣ፣

እስረኞችሽን ውሃ ከሌለበት ጕድጓድ ነጻ እለቅቃቸዋለሁ።

12እናንት በተስፋ የምትኖሩ እስረኞች፤ ወደ ምሽጎቻችሁ ተመለሱ፤

አሁንም ቢሆን ሁለት ዕጥፍ አድርጌ እንደምመልስላችሁ እናገራለሁ።

13ቀስቴን እንደ ገተርሁ፣ ይሁዳን እገትረዋለሁ፤

ኤፍሬምንም ፍላጻ አደርገዋለሁ።

ጽዮን ሆይ፤ ልጆችሽን አስነሣለሁ፤

ግሪክ ሆይ፤ በአንቺ ልጆች ላይ ይነሣሉ፤

እንደ ተዋጊ ሰይፍም አደርግሻለሁ።

እግዚአብሔር ይገለጣል

14እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ይገለጣል፤

ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፤

ጌታ እግዚአብሔር መለከት ይነፋል፤

በደቡብም ዐውሎ ንፋስ ውስጥ ይጓዛል፤

15እግዚአብሔር ጸባኦትም ይከልላቸዋል፤

ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤

በድንጋይ ወንጭፍም ያሸንፋሉ፤

ይጠጣሉ፤ በወይን ጠጅ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤

የመሠዊያውን ማእዘኖች ለመርጨት፣

እንደ ተዘጋጀ ዕቃ9፥15 ወይም ጽዋ፣ እነርሱም እንደዚሁ ተሞልተዋል።

16ሕዝቡን የራሱ መንጋ አድርጎ

በዚያ ቀን አምላካቸው እግዚአብሔር ያድናቸዋል።

በአክሊል ላይ እንዳለ ዕንቍ፣

በገዛ ምድሩ ላይ ያብለጨልጫሉ።

17እንዴት ውብና አስደናቂ ይሆናሉ፤

እህል ጕልማሶችን፣

አዲስ የወይን ጠጅም ቈነጃጅትን ያሳምራል።