ዘካርያስ 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘካርያስ 11:1-17

1ሊባኖስ ሆይ፤ እሳት ዝግባሽን እንዲበላው

ደጆችሽን ክፈቺ!

2የጥድ ዛፍ ሆይ፤ ዝግባ ወድቋልና አልቅስ፤

የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋል!

የባሳን ወርካዎች ሆይ፤ አልቅሱ፤

ጥቅጥቅ ያለው ደን ተመንጥሯል!

3የእረኞችን ዋይታ ስሙ፤

ክብራቸው ተገፍፏልና፤

የአንበሶችን ጩኸት ስሙ፤

ጥቅጥቅ ያለው የዮርዳኖስ ደን ወድሟል!

ሁለቱ እረኞች

4እግዚአብሔር አምላኬ እንዲህ ይላል፤ “ለዕርድ የተለዩትን በጎች አሰማራ፤ 5የገዟቸው ያርዷቸዋል፤ ሳይቀጡም ይቀራሉ፤ የሸጧቸውም፣ ‘እግዚአብሔር ይመስገን፤ ባለጠጋ ሆኛለሁ’ ይላሉ፤ ጠባቂዎቻቸውም እንኳ አይራሩላቸውም። 6ከእንግዲህ በምድሪቱ ለሚኖረው ሕዝብ አልራራምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያስጨንቃሉ፤ እኔም ከእጃቸው አላድናቸውም።”

7ስለዚህ ለዕርድ የተለዩትን በጎች፣ በተለይም የተጨቈኑትን አሰማራሁ። ሁለት በትሮች ወስጄም፣ አንዱን “ሞገስ” ሌላውንም “አንድነት” ብዬ ጠራኋቸው፤ መንጋውንም አሰማራሁ። 8በአንድ ወር ውስጥ ሦስቱን እረኞች አስወገድሁ።

በጎቹ ጠሉኝ፤ እኔም፣ ሰለቸኋቸው፤ 9“እረኛችሁ አልሆንም፤ የሚሞቱት ይሙቱ፤ የሚጠፉት ይጥፉ፤ የቀሩትም አንዱ የሌላውን ሥጋ ይብላ” አልኋቸው።

10ከዚያም ከአሕዛብ ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን ለማፍረስ፣ “ሞገስ” ብዬ የጠራሁትን በትሬን ወስጄ ሰበርሁት። 11በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ ሲመለከቱኝ የነበሩትና የተጨነቁት በጎችም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ዐወቁ።

12እኔም፣ “የሚበጅ መስሎ ከታያችሁ ዋጋዬን ክፈሉኝ፤ አይሆንም ካላችሁም ተዉት” አልኋቸው፤ ስለዚህ ሠላሳ ብር ከፈሉኝ።

13እግዚአብሔርም ሊከፍሉኝ የተስማሙበትን ጥሩ ዋጋ “በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው” አለኝ፤ እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው ግምጃ ቤት አስቀመጥሁት። 14ከዚያም የእስራኤልንና የይሁዳን ወንድማማችነት በማፍረስ፣ “አንድነት” ብዬ የጠራሁትን ሁለተኛውን በትሬን ሰበርሁት።

15እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “እንደ ገና የሰነፍ እረኛ ዕቃ ውሰድ፤ 16እነሆ፤ በምድሪቱ ላይ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፤ የባዘነውን አይፈልግም፤ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፤ ነገር ግን የሠባውን ሥጋ ይበላል፤ ሰኰናውንም ሳይቀር ይቀለጣጥማል።

17“መንጋውን ለሚተው፣

ለማይረባ እረኛ ወዮለት!

ሰይፍ ክንዱንና ቀኝ ዐይኑን ትውጋው!

ክንዱ ፈጽማ ትስለል!

ቀኝ ዐይኑም ጨርሳ ትታወር!”