ዘሌዋውያን 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘሌዋውያን 11:1-47

የተፈቀደና ያልተፈቀደ መብል

11፥1-23 ተጓ ምብ – ዘዳ 14፥3-20

1እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፤ ‘በየብስ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ የምትበሏቸው እነዚህ ናቸው፦ 3ሰኰናው የተሰነጠቀውን የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ።

4“ ‘የሚያመሰኩ ሆነው ሰኰናቸው ያልተሰነጠቀ ወይም ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ሆኖ የማያመሰኩትን አትብሉ፤ ግመል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 5ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 6ጥንቸል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 7ዐሳማ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 8የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ፤ ጥንባቸውንም አትንኩ፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሁኑ።

9“ ‘በባሕሮችና በወንዞች ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጡሮች ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን መብላት ትችላላችሁ፤ 10ነገር ግን በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ከሚኖሩት ፍጡሮች ሁሉ፣ ከሚንፏቀቁት ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ሌሎች ፍጡሮች መካከል ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ፤ 11በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆኑ ሥጋቸውን አትብሉ፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ፤ 12ክንፍና ቅርፊት የሌለው ማንኛውም በውሃ ውስጥ የሚኖር ፍጡር በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ይሁን።

13“ ‘ከአዕዋፍ ወገን እነዚህን ትጸየፋላችሁ፤ ጸያፍ ስለ ሆኑም አትብሏቸው፦ ንስር፣ ጥንብ አንሣ፣ ግልገል አንሣ፣ 14ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፣ 15ማንኛውም ዐይነት ቍራ፣ 16ሰጐን፣ ጠላቋ፣ ዝይ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣ 17ጕጕት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣ 18የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ስደተኛ አሞራ፣ 19ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ።11፥19 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያሉ የእያንዳንዱ አዕዋፍ፣ ነፍሳትና እንስሳት ትክክለኛ ማንነታቸው በትክክል አይታወቅም

20“ ‘ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ። 21ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ። 22ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ። 23ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው።

24“ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 25የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።

26“ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል። 27አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 28የእነዚህን በድን የሚያነሣ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንስሳቱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው።

29“ ‘ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፦ ሙጭልጭላ፣ ዐይጥ፣ እንሽላሊት በየወገኑ፣ 30ዔሊ፣ ዐዞ፣ ገበሎ፣ አርጃኖ፣ ዕሥሥት። 31ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሁሉ መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ ከእነዚህም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 32በድኑ በማንኛውም ዕቃ ላይ ቢወድቅ ያ ዕቃ ከዕንጨት፣ ከጨርቅ፣ ከቈዳ ወይም ከበርኖስ የተሠራ ቢሆን ርኩስ ይሆናል፤ በውሃ ውስጥ ይደረግ፤ ሆኖም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33በድኑም በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፣ በውስጡ ያለ ነገር ሁሉ ርኩስ ስለሚሆን ዕቃውን ስበሩት። 34ማንኛውም ምግብ እንዲህ ካለው ዕቃ ውሃ ቢፈስስበት ይረክሳል፤ ከዚህ ዕቃ የሚጠጣውም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው። 35ከበድናቸው አንዱ የወደቀበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ምድጃም ይሁን ማሰሮ ይሰበር፤ ርኩሳን ናቸው፤ እናንተም ተጸየፏቸው። 36ነገር ግን ምንጭ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ንጹሕ እንደ ሆነ ይቈያል፤ ሆኖም በድኑን የነካ ይረክሳል። 37በሚዘራ ዘር ላይ በድን ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ እንደ ሆነ ይቈያል። 38ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ በድን ቢወድቅበት ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።

39“ ‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳት አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 40ማንም ሰው ከበድኑ ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

41“ ‘ምድር ለምድር የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡር ጸያፍ ነው፤ አይበላም። 42ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጡር ሁሉ፣ ይኸውም በደረቱ የሚሳበውን ወይም በአራት እግር የሚሄደውን ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን አትብሉ፤ ጸያፍ ነው። 43በእነዚህ ፍጡራን ሁሉ ራሳችሁን አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነርሱም ራሳችሁን በማጕደፍ አትርከሱ። 44እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ተለዩ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ ምድር ለምድር በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ፍጡር ራሳችሁን አታርክሱ። 45አምላካችሁ (ኤሎሂም) እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።

46“ ‘እንስሳትንና አዕዋፍን፣ በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ሁሉ በሚመለከት የተሰጠ ሕግ ይህ ነው። 47በዚህም በርኩሱና በንጹሑ መካከል፣ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጡራን የሚበሉትንና የማይበሉትን ትለያላችሁ።’ ”