ዕብራውያን 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዕብራውያን 10:1-39

ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕት

1ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ እውነተኛው አካል አይደለም፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር ያለ ማቋረጥ የሚቀርበው ተደጋጋሚ መሥዋዕት፣ ለአምልኮ የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም። 2ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር። 3ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤ 4ምክንያቱም የኰርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም።

5ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤

“መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤

ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤

6በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት

በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም።

7በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣

አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ።’ ”10፥7 ሰብዓ ሊቃናት ይመ።

8ሕጉ ይህ እንዲደረግ ቢያዝም፣ እርሱ ግን በመጀመሪያ፣ “መሥዋዕትንና መባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ ደስም አልተሰኘህበትም” ይላል። 9ቀጥሎም፣ “እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ፤ ሁለተኛውን ለመመሥረት የመጀመሪያውን ሻረ። 10በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል።

11ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል። 12ይህኛው ካህን ግን አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፤ 13ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤ 14ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጓቸዋል።

15መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤ 16“ከዚያም በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤

ይላል ጌታ፤

ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤

በአእምሯቸውም እጽፈዋለሁ።”

17ደግሞም፣

“ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣

ከእንግዲህ አላስብም” ይላል።

18እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም።

እስከ መጨረሻው ጸንቶ ስለ መገኘት የቀረበ ጥሪ

19እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ 20ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው። 21በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን፣ 22ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። 23የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ። 24እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። 25አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።

26የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤ 27የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው። 28የሙሴን ሕግ የናቀ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይገደል ነበር። 29ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቈጠረ፣ የጸጋንም መንፈስ ያክፋፋ እንደ ምን ያለ የባሰ ቅጣት ይገባው ይመስላችኋል? 30“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ደግሞም፣ “ጌታ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል። 31በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው።

32ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ፣ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ ጸንታችሁ የቆማችሁበትን የቀድሞውን ዘመን አስቡ። 33አንዳንድ ጊዜ በአደባባይ ለስድብና ለስደት ተጋልጣችሁ ነበር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ያለ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር አብራችሁ መከራን ተቀብላችኋል። 34እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ።

35ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። 36የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ የተስፋ ቃሉን እንድትቀበሉ፣ ጸንታችሁ መቆም ያስፈልጋችኋል፤ 37ምክንያቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣

“የሚመጣው እርሱ ይመጣል፤ አይዘገይም።

38ጻድቅ ግን10፥38 ወይም የእኔ ጽድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤

ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣

ነፍሴ በእርሱ ደስ አትሰኝም።”

39እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም።