ልጁ ከመላእክት በላይ ነው
1እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ 2በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። 3እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። 4ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኗል።
5እግዚአብሔር፣
“አንተ ልጄ ነህ፤
እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤”1፥5 ወይም እኔ ዛሬ አባት ሆንሁህ
ወይስ ደግሞ፣
“እኔ አባት እሆነዋለሁ፤
እርሱም ልጅ ይሆነኛል”
ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 6ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣
“የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ1፥6 የሙት ባሕር ጥቅልሎችንና ሰብዓ ሊቃናትን ይመ ይስገዱለት” ይላል።
7ስለ መላእክትም ሲናገር፣
“መላእክቱን ነፋሳት፣
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል” ይላል።
8ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤
“አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤
ጽድቅም የመንግሥትህ በትር ይሆናል፤
9ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣
የደስታንም ዘይት ቀባህ።”
10ደግሞም እንዲህ ይላል፤
“ጌታ ሆይ፤ አንተ
በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤
ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው።
11እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤
ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤
12እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤
እንደ ልብስም ይለወጣሉ።
አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤
ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”
13እግዚአብሔር፣
“ጠላቶችህን የእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ”
ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 14መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?