ኤርምያስ 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 7:1-34

ዋጋ ቢስ አምልኮ

1ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ 2በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ በዚያም ይህን መልእክት ዐውጅ፤

እግዚአብሔርን ለማምለክ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሕዝብ ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘መንገዳችሁንና ሥራችሁን አስተካክሉ፤ እኔም በዚህ ስፍራ እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ።’ 4ይህ ‘የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ’ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ። 5መንገዳችሁንና ሥራችሁን በርግጥ ብታሳምሩ፣ በመካከላችሁ ቅንነት ቢኖር፣ 6መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈስሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣ 7ለአባቶቻችሁ ለዘላለም ርስት አድርጌ በሰጠኋቸው ምድር፣ በዚህ ስፍራ አኖራችኋለሁ። 8እናንተ ግን፣ ከንቱ በሆኑ የሐሰት ቃላት ታምናችኋል።

9“ ‘ትሰርቃላችሁ፤ ሰው ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ በሐሰት ትምላላችሁ፤7፥9 ወይም በሐሰተኛ አማልክት ትሞላላችሁ ለበኣል ታጥናላችሁ፤ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ትከተላላችሁ፤ 10ስሜ ወደሚጠራበት ወደዚህ ቤት መጥታችሁ በፊቴ ትቆሙና “ደኅና ነን” እያላችሁ እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ታደርጋላችሁ። 11ስሜ የሚጠራበት፣ ይህ ቤት በእናንተ ዘንድ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኗልን? እነሆ፤ የምታደርጉትን ነገር አይቻለሁ ይላል እግዚአብሔር

12“ ‘እንግዲህ ቀድሞ የስሜ ማደሪያ አድርጌው ወደ ነበረው ስፍራ ወደ ሴሎ ሂዱ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትንም እዩ። 13እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም። 14ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ አሁንም ስሜ በተጠራበት ቦታ፣ በታመናችሁበት ቤተ መቅደስ፣ ለአባቶቻችሁና ለእናንተ በሰጠሁት በዚህ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ። 15ወንድሞቻችሁ የሆኑትን፣ የኤፍሬምን ሁሉ ሕዝብ እንዳስወገድሁ፣ እናንተንም ከፊቴ እጥላችኋለሁ።’

16“እንግዲህ ስለማልሰማህ፣ ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን፤ አትማልድላቸውም። 17እነርሱ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? 18ለሰማይዋ ንግሥት ቂጣ ሊጋግሩ፣ ልጆች ዕንጨት ይለቅማሉ፤ አባቶች እሳት ያቀጣጥላሉ፤ ሴቶችም ሊጥ ያቦካሉ፤ ሊያስቈጡኝም ለሌሎች አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያቀርባሉ። 19ለመሆኑ ይህን የሚያደርጉት እኔን ለማስቈጣት ነውን? ይላል እግዚአብሔር፤ ይልቁን ይህን በማድረጋቸው በሚደርስባቸው ዕፍረት የሚጐዱት ራሳቸውን አይደለምን?

20“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ በሰውና በእንስሳ ላይ፣ በዱር ዛፍና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።”

21“ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሚቃጠል መሥዋዕታችሁን በሌሎች መሥዋዕታችሁ ላይ ጨምሩ፤ ሥጋውንም ራሳችሁ ብሉ። 22የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብፅ ባወጣኋቸው ጊዜ፣ ስለ መሥዋዕቶችና ስለሚቃጠል መሥዋዕት አልተናገርኋቸውም፤ ትእዛዝም አልሰጠኋቸውም። 23ነገር ግን ድምፄን ስሙ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቤ ትሆናላችሁ፤ መልካም እንዲሆንላችሁም፣ ባዘዝዃችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ አዘዝኋቸው። 24እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብ ብለው ለማድመጥም አልፈለጉም፤ ይልቁን የክፉ ልባቸውን ሐሳብ በእልኸኝነት ተከተሉ፤ ወደ ፊት በመሄድ ፈንታም ወደ ኋላቸው ተመለሱ። 25አባቶቻችሁ ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በየቀኑ ሳላሠልስ አገልጋዮቼን ነቢያትን ላክሁባቸው። 26ሕዝቡ ግን አልሰማኝም፤ ልብ ብሎ ለማድመጥም አልፈለገም፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ አባቶቻቸው ከሠሩት የባሰም ክፉ አደረጉ።’

27“ይህን ሁሉ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱ ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፤ አይመልሱልህም። 28ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ይህ ሕዝብ አምላኩን እግዚአብሔርን ያልታዘዘ፣ ምክሩን ያልተቀበለ ወገን ነው፤ እውነት ጠፍቷል፤ ከአንደበታቸውም ሸሽቷል። 29እግዚአብሔር ቍጣው የወረደበትን ይህን ትውልድ ስለ ናቀውና ስለ ተወው፣ ጠጕርሽን ቈርጠሽ ጣዪ፤ በባድሞቹ ኰረብቶች ላይ ሆነሽም ሙሾ አውጪ።

የዕርድ ሸለቆ

30“ ‘የይሁዳ ሕዝብ በፊቴ ክፉ ነገር አድርጓል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ አስጸያፊ ነገራቸውን ስሜ በተጠራበት ቤት በማስቀመጥ አርክሰውታል። 31እኔ ያላዘዝኋቸውን፣ ከቶም ያላሰብሁትን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት አቃጥለው ለመሠዋት በሄኖም ልጅ ሸለቆ የቶፌትን መስገጃ ኰረብቶች ሠሩ። 32ስለዚህ አስተውሉ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ስፍራ እስከማይገኝ ድረስ ሙታንን በቶፌት ስለሚቀብሩ፣ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ተብሎ የማይጠራበት ጊዜ ይመጣል። 33የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም። 34የደስታና የተድላን ድምፅ፣ የሙሽራና የሙሽራዪቱን ድምፅ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም መንገዶች አጠፋለሁ፤ ምድሪቱ ባድማ ትሆናለችና።