ኤርምያስ 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 5:1-31

ቅን ሰው አለመገኘቱ

1“በኢየሩሳሌም መንገዶች እስቲ ውጡ፤ ወደ ላይ ወደ ታችም ውረዱ፤

ዙሪያውን ተመልከቱ ቃኙ፤

በአደባባይዋም ፈልጉ፤

እውነትን የሚሻና በቅንነት የሚሄድ፣

አንድ ሰው እንኳ ብታገኙ፣

እኔ ይህችን ከተማ እምራታለሁ።

2‘ሕያው እግዚአብሔርን!’ ቢሉም፣

የሚምሉት በሐሰት ነው።”

3እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህ እውነትን አይመለከቱምን?

አንተ መታሃቸው፤ እነርሱ ግን አልተሰማቸውም፤

አደቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን አልታረሙም፤

ፊታቸውን ከድንጋይ ይልቅ አጠነከሩ

በንስሓ ለመመለስም አልፈለጉም።

4እኔም በልቤ እንዲህ አልሁ፤ “እነዚህ ድኾች ናቸው፤

ሞኞች ናቸው፤

የእግዚአብሔርን መንገድ፣

የአምላካቸውን ሕግ አላወቁምና።

5ስለዚህ ወደ ታላላቆቹ እሄዳለሁ፤

ለእነርሱም እናገራለሁ፤

በርግጥ እነርሱ የእግዚአብሔርን መንገድ፣

የአምላካቸውንም ሕግ ያውቃሉና።”

ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ ያው እንደዚያው ቀንበሩን ሰብረዋል፤

እስራቱንም በጥሰዋል።

6ስለዚህ አንበሳ ከዱር ወጥቶ ይሰባብራቸዋል፣

የበረሓ ተኵላም ይቦጫጭቃቸዋል፤

ብቅ የሚለውን ሰው ሁሉ ለመገነጣጠል፣

ነብር በከተሞቻቸው ዙሪያ ያደባል፤

ዐመፃቸው ታላቅ፣

ክሕደታቸው ብዙ ነውና።

7“ታዲያ፣ እንዴት ይቅር ልልሽ እችላለሁ?

ልጆችሽ ትተውኛል፤

እውነተኛውን አምላክ ትተው አማልክት ባልሆኑት ምለዋል፤

እስኪጠግቡ ድረስ መገብኋቸው፤

እነርሱ ግን አመነዘሩ፤

ወደ ጋለሞቶችም ቤት ተንጋጉ።

8እንደ ተቀለበ ብርቱ ድንጉላ ፈረስ ሆኑ፤

እያንዳንዱም የሌላውን ሚስት ተከትሎ አሽካካ።

9ስለ እነዚህ ነገሮች አልቀጣቸውምን?”

ይላል እግዚአብሔር

“እኔ ራሴ እንደዚህ ዐይነቱን ሕዝብ

አልበቀልምን?

10“ወደ ወይን አትክልቷ ስፍራ ገብታችሁ አበላሹት፤

ነገር ግን ፈጽማችሁ አታጥፉት፤

ቅርንጫፎቿን ገነጣጥሉ፤

የእግዚአብሔር አይደሉምና፤

11የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት፣

ፈጽመው ከድተውኛል፤”

ይላል እግዚአብሔር

12በእግዚአብሔር ላይ ሐሰትን ተናገሩ፤

እንዲህም አሉ፤ “እሱ ምንም አያደርግም!

ክፉ ነገር አይደርስብንም፤

ሰይፍም ራብም አናይም፤

13ነቢያቱ ነፋስ እንጂ ሌላ ነገር አይደሉም፤

ቃሉም በውስጣቸው የለም፤

ያሉት ሁሉ በእነርሱ ላይ ይመለስ።”

14ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ሕዝቡ ይህን ቃል ስለ ተናገረ፣

ቃሌን በአፍህ ውስጥ የሚፋጅ እሳት፣

ይህንም ሕዝብ ማገዶ አደርጋለሁ፤

እሳቱም ይበላቸዋል፤

15የእስራኤል ቤት ሆይ፤” ይላል እግዚአብሔር

“ከሩቅ ሕዝብን አመጣባችኋለሁ፤

ጥንታዊና ብርቱ፣

ቋንቋውን የማታውቁት፣ ንግግሩንም

የማትረዱት ሕዝብ ነው።

16የፍላጻቸው ሰገባ እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤

ሁሉም ብርቱ ተዋጊዎች ናቸው።

17ሰብልህንና ምግብህን ጠራርገው ይበሉብሃል፤

ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን ይውጣሉ፤

በጎችህንና ከብቶችህን ይፈጃሉ፤

የወይን ተክሎችህንና የበለስ ዛፎችህን ያወድማሉ፤

የታመንህባቸውንም የተመሸጉ ከተሞች

በሰይፍ ያጠፏቸዋል።

18“ይሁን እንጂ፣ በዚያን ዘመን እንኳ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ፈጽሜ አላጠፋችሁም። 19ሕዝቡ፣ ‘እግዚአብሔር አምላካችን ይህን ሁሉ ነገር ለምን አደረገብን?’ ብለው ቢጠይቁ፣ ‘እኔን፣ እንደ ተዋችሁኝና በራሳችሁ ምድር ባዕዳን አማልክትን እንዳገለገላችሁ፣ እንደዚሁ የእናንተ ባልሆነ ምድር ባዕዳንን ታገለግላላችሁ’ ትላቸዋለህ።

20“በያዕቆብ ቤት ይህን አሰሙ፤

በይሁዳም እንዲህ ብላችሁ ዐውጁ፤

21እናንት ዐይን እያላችሁ የማታዩ፣

ጆሮ እያላችሁ የማትሰሙ፣

ሞኞችና የማታስተውሉ ሰዎች ይህን ስሙ፤

22ልትፈሩኝ አይገባችሁምን?” ይላል እግዚአብሔር

“በእኔ ፊት ልትንቀጠቀጡስ አይገባምን?

ለዘላለም ዐልፎት መሄድ እንዳይችል፣

አሸዋን ለባሕር ድንበር አደረግሁ፤

ማዕበሉ እየጋለበ ቢመጣ ከዚያ አያልፍም፤

ሞገዱ ቢጮኽም ሊያቋርጠው አይችልም።

23ይህ ሕዝብ ግን የሸፈተና እልኸኛ ልብ አለው፤

መንገድ ለቆ ሄዷል፤

24በልባቸውም፣

‘የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚያዘንበውን፣

መከርን በወቅቱ የሚያመጣልንን፣

አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ’ አላሉም።

25በደላችሁ እነዚህን አስቀርቶባችኋል።

ኀጢአታችሁ መልካሙን ነገር ከልክሏችኋል።

26“በሕዝቤ መካከል ክፉ ሰዎች አሉና፤

ወፍ እንደሚያጠምዱ ሰዎች፣

ወጥመድ ዘርግተው ሰው እንደሚይዙ ሰዎችም ያደባሉ።

27ወፎች እንደ ሞሉት ጐጆ፣

ቤታቸው በማጭበርበር የተሞላ ነው፤

ባለጠጎችና ኀያላን ሆነዋል፤

28ወፍረዋል፤ ሠብተዋልም።

ክፋታቸው ገደብ የለውም፤

ወላጅ የሌላቸው ፍትሕ እንዲያገኙ

አልቆሙላቸውም፤

ለድኾችም መብት አልተከራከሩም።

29ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?”

ይላል እግዚአብሔር

እንዲህ ዐይነቶቹን ሕዝብ፣

እኔ ራሴ ልበቀላቸው አይገባኝምን?

30“የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ ነገር

በምድሪቱ ላይ ሆኗል፤

31ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤

ካህናት በነቢያቱ ምክር ያስተዳድራሉ፤

ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ይወድዳሉ፤

ፍጻሜው ሲደርስ ግን ምን ታደርጉ ይሆን?”