ኤርምያስ 40 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 40:1-16

ኤርምያስ በነጻነት መኖሩ

1የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን ኤርምያስን ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ወደ ባቢሎን በሚወስዱት ምርኮኞች ሁሉ መካከል በራማ በሰንሰለት ታስሮ ባገኘው ጊዜ አስፈታው፤ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 2የዘበኞቹ አዛዥ ኤርምያስን ለብቻው ወስዶ፣ እንዲህ አለው፤ “አምላክህ እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ይህን ጥፋት ተናገረ፤ 3አሁንም እግዚአብሔር አመጣው፤ እንደ ተናገረውም አደረገ። ይህ ሁሉ የሆነው እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ስለ ሠራችሁና እርሱን ስላልታዘዛችሁ ነው። 4እነሆ፤ ዛሬ የእጅህን ሰንሰለት ፈታሁልህ። ከፈለግህ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን ና፤ እኔም እንከባ ከብሃለሁ፤ ካልፈለግህ ግን አትምጣ። እነሆ፤ አገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ደስ ወዳሰኘህ ሂድ።” 5ኤርምያስ ገና መልስ ሳይሰጥ40፥5 ወይም ኤርምያስ ሳይመልስ ናቡዘረዳን በመቀጠል፣ “የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፤ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል ተቀመጥ፤ ወይም ደስ ወዳሰኘህ ስፍራ ሂድ” አለው። የዘበኞቹ አዛዥ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው፤ 6ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ ምጽጳ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር በምድሪቱ በቀረው ሕዝብ መካከል ኖረ።

የጎዶልያስ መገደል

40፥7-941፥1-3 ተጓ ምብ – 2ነገ 25፥22-26

7በየሜዳው የነበሩት የጦር መኰንኖችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምድሪቱ ላይ ገዥ አድርጎ እንደ ሾመውና ወደ ባቢሎን በምርኮ ባልተወሰዱት በምድሪቱ ድኾች ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠው በሰሙ ጊዜ፣ 8ወደ ምጽጳ፣ ጎዶልያስ ዘንድ መጡ፤ የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያ ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፣ የተንሑት ልጅ ሠራያ፤ የነጦፋዊው የዮፌ ልጆች፣ የማዕካታዊ ልጅ ያእዛንያን40፥8 የዕብራይስጡ ያእዛንያን የያዛንያ አቻ ስም ነው። ሰዎቻቸውም ነበሩ። 9የሳፋን ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ሲል ቃል ገባላቸው፤ “ለባቢሎናውያን40፥9 ወይም ከለዳያን፤ 10 ይመ መገዛት አትፍሩ፤ በምድሪቱ ተቀምጣችሁ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ መልካም ይሆንላችኋል። 10እኔም ራሴ ወደ እኛ በሚመጡት በባቢሎናውያን ፊት ልቆምላችሁ፣ በምጽጳ እቀመጣለሁ፤ እናንተ ግን ወይን፣ የበጋ ፍሬና ዘይት አምርቱ፤ በማከማቻ ዕቃዎቻችሁ ውስጥ ክተቱ፤ በያዛችኋቸውም ከተሞች ተቀመጡ።”

11በሞዓብ፣ በአሞን፣ በኤዶምና በሌሎች አገሮች ሁሉ የነበሩ አይሁድ በሙሉ የባቢሎን ንጉሥ፣ ሰዎችን በይሁዳ እንዳስቀረና የሳፋን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመ በሰሙ ጊዜ፣ 12ሁላቸውም ከተበታተኑበት አገር ሁሉ ወደ ይሁዳ ምድር ተመለሱ፤ በምጽጳ ወደሚኖረውም ወደ ጎዶልያስ መጡ፤ ወይንና የበጋ ፍሬም በብዛት አከማቹ። 13የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ገና በየሜዳው የነበሩት የጦር መኰንኖች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ ምጽጳ መጥተው፣ 14“የአሞናውያን ንጉሥ በአሊስ አንተን ለመግደል የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ላከው አታውቅምን?” አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም።

15የቃሬያ ልጅ ዮሐናን፣ “ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ሄጄ ልግደለው፤ ሸሽተው ወደ አንተ የመጡት አይሁድ እንዲበተኑ፣ በይሁዳም የቀሩት እንዲጠፉ ለምን ይገድልሃል?” ብሎ በምጽጳ ለጎዶልያስ በምስጢር ነገረው።

16የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን፣ “ስለ እስማኤል የምትነግረኝ ሁሉ እውነት አይደለምና ይህን ነገር አታድርግ” አለው።