ኤርምያስ 25 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 25:1-38

ሰባ የምርኮ ዓመታት

1የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ይህም ማለት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያው ዓመት፣ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለኤርምያስ ቃል መጣለት፤ 2ስለዚህ ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩትም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ 3የይሁዳ ንጉሥ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ከነገሠበት ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሃያ ሦስት ዓመት ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ ደጋግሜም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም።

4እግዚአብሔር አገልጋዮቹን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሞ ወደ እናንተ ላከ፤ ሆኖም አልሰማችሁም፤ ትኵረትም አልሰጣችሁትም። 5እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እንግዲህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣት ምድር ለዘላለም ትቀመጣላችሁ። 6ታገለግሏቸውና ታመልኳቸው ዘንድ ሌሎቹን አማልክት አትከተሉ፤ እጃችሁ በሠራው ነገር አታስቈጡኝ፤ እኔም ክፉ አላደርግባችሁም።”

7“ነገር ግን አልሰማችሁኝም” ይላል እግዚአብሔር፤ “እጃችሁ በሠራው ነገር አስቈጣችሁኝ፤ በራሳችሁም ላይ ክፉ ነገር አመጣችሁ።”

8ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃሌን ስላልሰማችሁ፣ 9የሰሜንን ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤25፥9 አጠፋቸዋለሁ ለሚለው የሚተካው የዕብራይስጥ ቃል የሚያመለክተው ነገሮች ወይም ሰዎች (ደግሞ ላይመለሱ) ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መሰጠታቸውን ነው። ሰዎች የሚጸየፏቸውና የሚሣለቁባቸው፣ የዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ፤ 10የደስታንና የእልልታን ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ፣ የወፍጮን ድምፅና የመብራትን ብርሃን አስቀራለሁ። 11አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።

12“ነገር ግን ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ሕዝቡን፣ የባቢሎናውያንንም25፥12 ወይም ከለዳውያን ምድር ስለ በደላቸው እቀጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለዘላለምም ባድማ አደርጋታለሁ፤ 13በምድሪቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ ይኸውም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኤርምያስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ የተናገረውን ትንቢት አመጣባታለሁ። 14ሕዝቧም ለብዙ ሕዝቦችና ለታላላቅ ነገሥታት ባሮች ይሆናሉ፤ እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸውም ሥራ እከፍላቸዋለሁ።”

የቍጣው ጽዋ

15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “በቍጣዬ የወይን ጠጅ የተሞላውን ይህን ጽዋ ከእጄ ውሰድ፤ እኔ ወደምልክህም ሕዝቦች ሁሉ ሄደህ አጠጣቸው። 16በጠጡም ጊዜ ይንገዳገዳሉ፤ በመካከላቸው ከምሰድደው ሰይፍ የተነሣ ያብዳሉ።”

17ስለዚህ ጽዋውን ከእግዚአብሔር እጅ ተቀብዬ እርሱ ወደ ላከኝ ሕዝቦች ሁሉ ሄድሁ፤ እንዲጠጡትም አደረግሁ፤ 18ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና ሰዎች የሚጸየፏቸው መዘባበቻና ርግማን እንዲሆኑ፣ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች፣ ነገሥታቷንና ባለሥልጣኖቿን፣ 19የግብፅን ንጉሥ ፈርዖንን፣ አገልጋዮቹን፣ ባለሥልጣኖቹንና ሕዝቡን ሁሉ፣ 20በዚያ የሚኖሩትን ድብልቅ ሕዝብ ሁሉ፣ የዖፅ ምድር ነገሥታትን ሁሉ፣ በአስቀሎና፣ በጋዛ፣ በአቃሮንና በአዛጦንም ሕዝብ ቅሬታ ያሉትን የፍልስጥኤም ነገሥታት፣ 21ኤዶምን፣ ሞዓብን፣ አሞንን፣ 22የጢሮስንና የሲዶናን ነገሥታት ሁሉ፣ ከባሕሩ ማዶ ያሉ የጠረፍ ምድር ነገሥታትን፣ 23ድዳንን፣ ቴማንን፣ ቡዝን፣ ጠጕራቸውን ዙሪያውን የሚከረከሙትን ሕዝብ ሁሉ፣25፥23 ወይም በሩቅ ስፍራዎች ያሉትን 24የዐረብ ነገሥታትን ሁሉ፣ በምድረ በዳ የሚኖሩትን የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታት ሁሉ፣ 25የዘምሪ፣ የኤላምና የሜዶን ነገሥታትን ሁሉ፣ 26በቅርብና በሩቅ ያሉትን የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ በማከታተል፣ በምድር ላይ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ አጠጣኋቸው፤ ከእነዚህም ሁሉ በኋላ የሺሻክ25፥26 ሺሻክ የባቢሎን ምስጢራዊ ቃል ነው። ንጉሥ ደግሞ ይጠጣል።

27“አንተም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጠጡ፤ ስከሩ፤ አስታውኩም፤ ዳግመኛም ላትነሡ በመካከላችሁ በምሰድደው ሰይፍ ፊት ውደቁ።” 28ነገር ግን ጽዋውን ከእጅህ ለመውሰድና ለመጠጣት እንቢ ካሉ፣ እንዲህ በላቸው፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግድ ትጠጣላችሁ። 29እነሆ፤ ስሜ የተጠራበትን ከተማ ማጥፋት እጀምራለሁ፤ ታዲያ ያለ ቅጣት ታመልጣላችሁን? ሳትቀጡ አትለቀቁም፤ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ሳትቀጡ አታመልጡም፤” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’

30“እንግዲህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገርባቸው፤ እንዲህም በላቸው፣

“ ‘እግዚአብሔር ከላይ ይጮኻል፤

ከቅዱስ ማደሪያው ነጐድጓዳማ ድምፁን ያሰማል፤

በራሱ ምድር ላይ እጅግ ይጮኻል፤

እንደ ወይን ጨማቂዎች፣

በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይም ያስገመግማል፤

31እግዚአብሔር ከሕዝቦች ጋር ይፋረዳልና፣

ታላቅ ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ያስተጋባል፤

በሰው ሁሉ ላይ ፍርድን ያመጣል፤

ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል’ ”

ይላል እግዚአብሔር

32የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ ጥፋት፣

ከአገር ወደ አገር እየተዛመተ መጥቷል፤

ብርቱ ዐውሎ ነፋስ፣

ከምድር ዳርቻ ተነሥቷል።”

33በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ፤ እንደ ጕድፍ በምድር ላይ ይጣላሉ እንጂ፣ አይለቀስላቸውም፤ ሬሳቸውም አይሰበሰብም፤ አይቀበርምም።

34እናንት እረኞች፤ አልቅሱ፤ ዋይ በሉ፤

እናንት የመንጋው ጌቶች፤ በዐመድ ላይ ተንከባለሉ፤

የምትታረዱበት ቀን ደርሷልና፤

እንደ ውብ የሸክላ ዕቃ ወድቃችሁ ትከሰከሳላችሁ።

35እረኞች የሚሸሹበት፣

የመንጋ ጠባቂዎችም የሚያመልጡበት የለም።

36እግዚአብሔር ማሰማሪያቸውን አጥፍቷልና፣

የእረኞችን ጩኸት፣

የመንጋ ጠባቂዎችን ዋይታ ስሙ።

37ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ፣

ሰላማዊው ምድር ባድማ ይሆናል።

38እንደ አንበሳ ከጐሬው ይወጣል፤

ከአስጨናቂው ሰይፍ፣25፥38 አንዳንድ የዕብራይስጥና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች (ኤር 46፥16 እና 50፥16 ይመ) ቍጣ ይላሉ።

ከቍጣውም የተነሣ፣

ምድራቸው ባድማ ትሆናለች።