ኤርምያስ 22 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 22:1-30

በክፉዎች ነገሥታት ላይ የተሰጠ ፍርድ

1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት ውረድ፤ ይህንም መልእክት በዚያ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ 2‘በዳዊት ዙፋን የተቀመጥህ፣ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተና መኳንንትህ፣ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ። 4እነዚህን ትእዛዞች በሚገባ ብትጠብቁ፣ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት፣ ከመኳንንታቸውና ከሕዝባቸው ጋር በሠረገሎችና በፈረሶች ተቀምጠው በዚህ ቤተ መንግሥት በሮች ይገባሉ፤ ይወጣሉም። 5ነገር ግን እነዚህን ትእዛዞች ባትጠብቁ፣ ይህ ቤተ መንግሥት እንዲወድም በራሴ ምያለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።’ ”

6ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት እንዲህ ይላል፤

“አንተ ለእኔ እንደ ገለዓድ፣

እንደ ሊባኖስ ተራራ ጫፍ ውብ ብትሆንም፣

በርግጥ እንደ ምድረ በዳ፣

ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች አደርግሃለሁ።

7በነፍስ ወከፍ መሣሪያ የሚይዙትን፣

አጥፊዎችን በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ።

ምርጥ የዝግባ ዛፎችን ይቈርጣሉ፤

ወደ እሳትም ይጥሏቸዋል።

8“ከተለያየ አገር የመጡ ሕዝቦች በዚህች ከተማ በኩል ሲያልፉ፣ ‘እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ላይ ለምን እንዲህ አደረገ?’ እያሉ እርስ በርስ ይነጋገራሉ፤ 9ከዚያም፣ ‘የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ኪዳን ትተው ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው’ ይላሉ።”

10ከእንግዲህ ስለማይመለስ፣

የተወለደባትንም ምድር ዳግመኛ ስለማያይ፣

ለተማረከው ንጉሥ አምርራችሁ አልቅሱ እንጂ፣

ቀድሞ ለሞተው አታልቅሱ፤ አትዘኑም።

11በአባቱ ምትክ በይሁዳ ላይ ስለ ነገሠው፣ ከዚህ ስፍራ በምርኮ ስለ ተወሰደው፣ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎ22፥11 ኢዮአካዝ ተብሎም ይጠራል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “ከእንግዲህ አይመለስም፤ 12ተማርኮ በሄደበት አገር ይሞታል እንጂ ይህችን ምድር ዳግመኛ አያይም።”

13“ቤተ መንግሥቱን በግፍ ለሚሠራ፣

ሰገነቱንም ፍትሕ በማዛባት ለሚገነባ፣

ወገኑን በነጻ ለሚያሠራ፣

የድካሙንም ዋጋ ለማይከፍለው፣

14‘ባለ ትልልቅ ሰገነት፣

ሰፊ ቤተ መንግሥት ለራሴ እሠራለሁ’ ለሚል ወዮለት!

ሰፋፊ መስኮቶችን ያበጅለታል፤

በዝግባ ዕንጨት ያስጌጠዋል፤

ቀይ ቀለምም ይቀባዋል።

15“በዝግባ ዕንጨት ብዛት፣

የነገሥህ ይመስልሃልን?

አባትህስ ፍትሕንና ጽድቅን በማድረጉ፣

የሚበላውና የሚጠጣው ጐድሎት ነበርን?

እነሆ፤ ሁሉም መልካም ሆነለት።

16የድኾችንና የችግረኞችን ፍትሕ አላጓደለም፤

ስለዚህም ሁሉ መልካም ሆነለት።

እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለምን?”

ይላል እግዚአብሔር

17“የአንተ ዐይንና ልብ ያረፉት ግን፣

አጭበርብሮ ጥቅምን በማግኘት፣

የንጹሑን ደም በማፍሰስ፣

ጭቈናንና ግፍን በመሥራት ላይ ብቻ ነው።”

18ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፤

“ ‘ዋይ ወንድሜ! ዋይ፣ እኅቴን!’

ብለው አያለቅሱለትም።

‘ዋይ፣ ጌታዬን! ዋይ፣ ለግርማዊነቱ!’

ብለውም አያለቅሱለትም።

19አህያ እንደሚቀበር ይቀበራል፤

ከኢየሩሳሌም በሮች ውጪ፤

ተጐትቶ ይጣላል።

20“ሊባኖስ ላይ ወጥተሽ ጩኺ፤

ድምፅሽን በባሳን አሰሚ፤

በዓባሪም ሆነሽ ጩኺ፤

ወዳጆችሽ ሁሉ ወድመዋልና።

21ተመችቶሽ በነበረ ጊዜ አስጠነቀቅሁሽ፤

አንቺ ግን፣ ‘አልሰማም’ አልሽ፤

ከትንሽነትሽ ጀምሮ መንገድሽ ይኸው ነበር፤

ቃሌንም አልሰማሽም።

22እረኞችሽ ሁሉ በነፋስ ይወሰዳሉ፤

ወዳጆችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤

ከክፋትሽም ሁሉ የተነሣ፣

ታፍሪያለሽ፤ ትዋረጂያለሽም።

23አንቺ፣ ‘በሊባኖስ’22፥23 ሊባኖስ የተባለው በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መንግሥት ነው (1ነገ 7፥23 ይመ)። ውስጥ የምትኖሪ፣

መኖሪያሽን በዝግባ ዛፍ የሠራሽ ሆይ፤

ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣

መከራ በላይሽ ሲመጣ ጩኸትሽ እንዴት ይሆን!

24“በሕያውነቴ እምላለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር “የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን22፥24 በዕብራይስጥ ኮንያ ሲሆን የኢዮአኪን አቻ ስም ቃል ነው፤ 28 ይመ። የቀኝ እጄ የቀለበት ማኅተም ብትሆን እንኳ ኖሮ፣ አውልቄ እጥልሃለሁ፤ 25ሕይወትህን ለሚሿት፣ ለምትፈራቸው ለባቢሎናውያንና22፥25 ወይም ከለዳውያን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 26አንተንና የወለደችህን እናትህን ወዳልተወለዳችሁበት ወደ ሌላ አገር ወርውሬ እጥላችኋለሁ፤ በዚያም ትሞታላችሁ። 27ልትመለሱባት ወደ ምትናፍቋት ምድር ከቶ አትመለሱም።”

28ይህ ኢኮንያን የተባለ ሰው፣ የተናቀና የተሰበረ ገንቦ፣

ማንም የማይፈልገው ዕቃ ነውን?

እርሱና ልጆቹ ለምን ወደ ውጪ ተጣሉ?

ወደማያውቁትስ ምድር ለምን ተወረወሩ?

29ምድር ሆይ፤ አንቺ ምድር፣ አንቺ ምድር፤

የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ!

30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“አንድ እንኳ የረባ ዘር የማይወጣለት፣

አንድ እንኳ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጥ፣

ወይም በይሁዳ የሚገዛ የማይኖረው ነውና፤

በሕይወት ዘመኑ የማይከናወንለት፣

መካን ሰው ብላችሁ መዝግቡት።”