ኢዮብ 29 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዮብ 29:1-25

1ኢዮብም እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፤

2“በእግዚአብሔር የተጠበቅሁበትን ዘመን፣

ያለፈውንም ወራት ምንኛ ተመኘሁ!

3ያን ጊዜ መብራቱ በራሴ ላይ ይበራ ነበር፤

በብርሃኑም በጨለማ ውስጥ ዐልፌ እሄድ ነበር፤

4እኔም ብርቱ ነበርሁ፤

የእግዚአብሔርም ወዳጅነት ቤቴን ይባርክ ነበር፤

5ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ነበረ፤

ልጆቼም በዙሪያዬ ነበሩ፤

6መንገዴ በቅቤ የራሰ ነበር፤

ዐለቱም የወይራ ዘይት ያመነጭልኝ ነበር።

7“ወደ ከተማዪቱ በር ብቅ ባልሁ ጊዜ፣

በአደባባይዋም በወንበር በተቀመጥሁ ጊዜ፣

8ጐበዛዝት አይተውኝ ገለል ይሉ፣

ሽማግሌዎችም ተነሥተው ይቆሙ ነበር።

9የሰፈሩ ታላላቅ ሰዎች ከመናገር ይቈጠቡ፣

እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር፤

10የመኳንንት ድምፅ ጸጥ ይል፣

ምላሳቸውም ከላንቃቸው ጋር ይጣበቅ ነበር፤

11የሰሙኝ ሁሉ ያሞጋግሱኝ፣

ያዩኝም ያመሰግኑኝ ነበር፤

12ለርዳታ የሚጮኸውን ችግረኛ፣

ድኻ ዐደጉንም ታድጌአለሁና።

13በሞት አፋፍ ላይ የነበረ መርቆኛል፤

የመበለቲቱንም ልብ አሳርፌአለሁ።

14ጽድቅን እንደ ልብስ ለበስሁ፤

ፍትሕም መጐናጸፊያዬና ጥምጥሜ ነበር።

15ለዕውራን ዐይን፣

ለዐንካሶችም እግር ነበርሁ።

16ለችግረኛው አባት፣

ለባይተዋሩ ተሟጋች ነበርሁ።

17የኀጢአተኛውን ክራንቻ ሰበርሁ፤

የነጠቀውንም ከጥርሶቹ አስጣልሁ።

18“እኔም በልቤ እንዲህ አልሁ፤ ‘ዘመኔ እንደ አሸዋ በዝቶ፣

በቤቴ ተደላድዬ እሞታለሁ፤

19ሥሬ ወደ ውሃ ይዘረጋል፤

ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤

20ክብሬ በውስጤ አዲስ እንደ ሆነ፣

ቀስትም በእጄ እንደ በረታ ይኖራል።’

21“ሰዎች ምክሬን በጸጥታ በመጠባበቅ፣

በጕጕት አደመጡኝ።

22እኔ ከተናገርሁ በኋላ፣ የሚናገር ሰው አልነበረም፤

ቃሌም እየተንጠባጠበ በጆሯቸው ይገባ ነበር።

23ዝናብ እንደሚጠብቅ ሰው ጠበቁኝ፤

ቃሌንም እንደ በልግ ዝናብ ጠጡ፤

24በሣቅሁላቸው ጊዜ እውነት አልመሰላቸውም፤

የፊቴም ብርሃን ብርቃቸው29፥24 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ነበር።

25መንገድ መርጬላቸው አለቃቸው ሆኜ ተቀመጥሁ፤

በሰራዊትም መካከል እንዳለ ንጉሥ ኖርሁ፤

ሐዘንተኞችንም እንደሚያጽናና ነበርሁ።