New Amharic Standard Version

ኢዩኤል 3:1-21

የተፈረደባቸው ሕዝቦች

1በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣

የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣

2አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤

ወደ ኢዮሣፍጥም3፥2 ኢዮሣፍጥ፣ የስሙ ትርጒም እግዚአብሔር ይፈርዳል ማለት ነው፤ ቍ 12 ላይም እንዲሁ። ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤

ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣

በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤

ምድሬን ከፋፍለዋል፤

ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና።

3በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤

ወንዶች ልጆችን በዝሙት አዳሪዎች ለወጡ፤

ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣

ሴቶች ልጆችን ሸጡ።

4“ጢሮስና ሲዶና እንዲሁም እናንተ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሁሉ ሆይ፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ምን አላችሁ? ስላደረግሁት ነገር ብድር ልትመልሱልኝ ነውን? የምትመልሱልኝ ከሆነ፣ በፍጥነትና በችኰላ እናንተ ያደረጋችሁትን በራሳችሁ ላይ መልሼ አደርግባችኋለሁ። 5ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤ የተመረጠውንም ንብረቴን ተሸክማችሁ ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አስገብታችኋልና። 6ከገዛ ምድራቸው ልታርቋቸው፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ለግሪኮች ሸጣችኋቸው።

7“እነሆ፤ እነርሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች አነሣሣቸዋለሁ፤ እናንተም ያደረጋችሁትን በገዛ ራሳችሁ ላይ እመልስባችኋለሁ። 8ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሰዎች ሸጣለሁ፤ እነርሱም መልሰው በሩቅ ላሉት ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።

9በሕዝቦች መካከል ይህን ዐውጁ፤

ለጦርነት ተዘጋጁ፤

ተዋጊዎችን አነሣሡ፤

ጦረኞችም ሁሉ ቀርበው ያጥቁ።

10ማረሻችሁ ሰይፍ፣

ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት፤

ደካማውም ሰው፣

“እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።

11እናንት በዙሪያ ያላችሁ ሕዝቦች ሁላችሁ፤

ፈጥናችሁ ኑ፤ በዚያም ተሰብሰቡ።

እግዚአብሔር ሆይ፤ ተዋጊዎችህን ወደዚያ አውርድ!

12“ሕዝቦች ይነሡ፤

ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ ፈጥነው ይውረዱ፤

ዙሪያውን ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ላይ ልፈርድ፣

በዚያ እቀመጣለሁና።

13ማጭዱን ስደዱ፤

መከሩ ደርሶአልና፤

ኑ ወይኑን ርገጡ፤

የወይን መጭመቂያው ሞልቶ፣

ከጒድጓዶቹም ተርፎ ፈሶአልና፤

ክፋታቸው እንደዚህ ታላቅ ነው።”

14ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ፣

ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ ተሰብስቦአል፤

ፍርድ በሚሰጥበት ሸለቆ፣

የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና።

15ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤

ከዋክብትም ከእንግዲህ አያበሩም።

16እግዚአብሔር ከጽዮን ጮኾ ይናገራል፤

ከኢየሩሳሌም ያንጐደጒዳል፤

ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤

እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣

ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።

በረከት ለእግዚአብሔር ሕዝብ

17“ከዚያም እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር

በቅዱሱ ተራራዬ በጽዮን እንደምኖር ታውቃላችሁ፤

ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ትሆናለች፤

ከእንግዲህም ወዲያ ባዕዳን አይወሯትም።

18“በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤

ኰረብቶችም ወተት ያፈሳሉ፤

በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎች3፥18 ወይም የሸጢም ሸለቆ ሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤

ከእግዚአብሔር ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤

የሰጢምን ሸለቆ ያጠጣል።

19ግብፅ ባድማ፣

ኤዶምም ምድረ በዳ ትሆናለች፤

በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ፣

በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ፈጽመዋልና።

20ይሁዳ ለዘላለም፣

ኢየሩሳሌምም ለትውልድ ሁሉ መኖሪያ ትሆናለች፤

21ደማቸውን እበቀላለሁ፤

በደለኛውንም ንጹሕ አላደርግም።”

እግዚአብሔር በጽዮን ይኖራል!