ኢሳይያስ 66 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 66:1-24

ፍርድና ተስፋ

1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ሰማይ ዙፋኔ ነው፤

ምድርም የእግሬ ማረፊያ ናት፤

ታዲያ የምትሠሩልኝ ቤት፣

የማርፍበትስ ስፍራ የቱ ነው?

2እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?

እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?”

ይላል እግዚአብሔር

“ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣

ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣

በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።

3ነገር ግን ወይፈን የሚሠዋልኝ፣

ሰው እንደሚገድል ነው፤

የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣

የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤

የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣

የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤

የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣

ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤

የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤

ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል።

4ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤

የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤

በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣

በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና።

በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤

የሚያስከፋኝንም መረጡ።”

5እናንት በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣

ይህን የእግዚአብሔር ቃል ስሙ፤

“እናንት ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣

ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣

‘እስቲ እግዚአብሔር ይክበርና፣

የእናንተን ደስታ እንይ’ አሏችሁ፤

ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።

6ያን የጩኸት ድምፅ ከከተማው ስሙ!

ያን ጫጫታ ከቤተ መቅደሱ ስሙ!

ይኸውም የእግዚአብሔር ድምፅ ነው፤

ለጠላቶቹም የሚገባቸውን ሁሉ ይከፍላቸዋል።

7“ከማማጧ በፊት፣

ትወልዳለች፤

በምጥ ጣር ከመያዟ በፊት፣

ወንድ ልጅ ትገላገላለች።

8እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል?

እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶ ያውቃል?

አገር በአንድ ጀንበር ይፈጠራልን?

ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል?

ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣

ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።

9ሊወለድ የተቃረበውን፣

እንዳይወለድ አደርጋለሁን?” ይላል እግዚአብሔር

“በሚገላገሉበት ጊዜስ፣

ማሕፀን እዘጋለሁን?” ይላል አምላክሽ።

10“ወዳጆቿ የሆናችሁ ሁሉ፣

ከኢየሩሳሌም ጋር ደስ ይበላችሁ፤

ስለ እርሷም ሐሤት አድርጉ፤

ለእርሷ ያለቀሳችሁ ሁሉ፣

ከእርሷ ጋር እጅግ ደስ ይበላችሁ።

11ከሚያጽናኑ ጡቶቿ፣

ትጠባላችሁ፤ ትረካላችሁም፤

እስክትረኩም ትጠጣላችሁ፤

በተትረፈረፈ ሀብቷም ትደሰታላችሁ።”

12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ ሰላምን እንደ ወንዝ ውሃ አፈስስላታለሁ፤

የመንግሥታትንም ብልጽግና እንደ ጅረት ውሃ አጐርፍላታለሁ፤

ትጠባላችሁ፤ በዕቅፏም ትያዛላችሁ፤

በጭኖቿም ላይ ትፈነድቃላችሁ።

13እናት ልጇን እሹሩሩ እንደምትል፣

እኔም እናንተን እሹሩሩ እላችኋለሁ፤

በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ።”

14ይህን ስታዩ፣ ልባችሁ ሐሤት ያደርጋል፤

ዐጥንቶቻችሁም እንደ ሣር ይለመልማሉ፤

የእግዚአብሔር እጅ ከባሮቹ ጋር መሆኑ ይታወቃል፤

ቍጣው ግን በጠላቶቹ ላይ ይገለጣል።

15እነሆ፤ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ይመጣል፤

ሠረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤

ንዴቱን በቍጣ፣

ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይገልጣል።

16በእሳትና በሰይፍ፣

እግዚአብሔር ፍርዱን በሰው ሁሉ ላይ ያመጣል፤

በእግዚአብሔር ሰይፍ የሚታረዱት ብዙ ይሆናሉ።

17“ወደ አትክልት ቦታዎች ለመሄድና ከተክሎቹ አንዱን ለማምለክ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የዕሪያዎችንና የዐይጦችን ሥጋ፣ የረከሱ ነገሮችንም የሚበሉ ሁሉ የመጨረሻ ፍርዳቸውን በአንድነት ይቀበላሉ” ይላል እግዚአብሔር

18“እኔም ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ መንግሥታትንና ልሳናትን ሁሉ ልሰበስብ እመጣለሁ፤66፥18 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። እነርሱም መጥተው ክብሬንም ያያሉ።

19“በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶባልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ። 20ለእግዚአብሔር ቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላል እግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቍርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል። 21እኔም ካህናትና ሌዋውያን ይሆኑ ዘንድ አንዳንዶቹን እመርጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር

22“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር23“ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር24“ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸው አይጠፋም፤ ለሰውም ዘር ሁሉ አስጸያፊ ይሆናሉ።”