ኢሳይያስ 65 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 65:1-25

ፍርድና ድነት

1“ላልለመኑኝ ራሴን ገለጥሁላቸው፤

ላልፈለጉኝ ተገኘሁላቸው።

ስሜን ላልጠራ ሕዝብ፣

‘አለሁልህ፤ አለሁልህ’ አልሁት።

2ለዐመፀኛ ሕዝብ፣

መልካም ባልሆኑ መንገዶች ለሚሄዱ፣

የልባቸውን ምኞት ለሚከተሉ፣

ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ።

ዘወትር በፊቴ የሚያስቈጡኝ ሕዝቦች፣

3በአትክልት ቦታዎች መሥዋዕት የሚያቀርቡ፣

በሸክላ መሠዊያዎች ላይ ዕጣን የሚያጥኑ፣

ዘወትር በፊቴ የሚያስቈጡኝ ሕዝብ ናቸው፤

4በመቃብር መካከል የሚቀመጡ፣

በስውር ቦታዎች የሚያድሩ፣

የዕሪያ ሥጋ የሚበሉ፣

ማሰሮዎቻቸውን በረከሰ ሥጋ መረቅ የሚሞሉ ናቸው፤

5‘ዘወር በል፤ አትቅረበኝ፤

አትጠጋኝ፤ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝ’ የሚሉ ናቸው።

እንዲህ ያለው ሕዝብ በአፍንጫዬ ዘንድ እንደ ጢስ፣

ቀኑን ሙሉ እንደሚነድድ እሳት ነው።

6“እነሆ፤ እንዲህ የሚል ተጽፎ በፊቴ ተቀምጧል፤

ዝም አልልም፤ ነገር ግን እንደ ሥራው እሰጠዋለሁ፤

የእጃቸውንም እከፍላቸዋለሁ፤

7የእናንተን ኀጢአት የአባቶቻችሁንም ኀጢአት እበቀላለሁ”

ይላል እግዚአብሔር

“በተራሮች ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ስላቀረቡ፣

በኰረብቶች ላይ ስለ ሰደቡኝ፣

በሰፈሩት ቍና ይሰፈርባቸዋል፤

ስለ ቀደሙት ሥራዎቻቸውም የእጃቸውን ያገኛሉ።”

8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“በወይኑ ዘለላ ውስጥ ጭማቂው ገና እንዳለ ሁሉ፣

ሰዎችም፣ ‘በውስጡ ጥሩ ነገር ስላለ

አትቍረጡት’ እንደሚሉ፣

እኔም ስለ ባሮቼ ስል እንዲሁ አደርጋለሁ፤

ሙሉ በሙሉ አላጠፋቸውም።

9ከያዕቆብ ዘር የሆኑትን፣

ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሱትን አመጣለሁ።

የተመረጠው ሕዝቤ ይወርሳቸዋል፤

ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ።

10አጥብቀው ለሚፈልጉኝ ሕዝቤ፣

ሳሮን የበጎች መሰማሪያ፣

የአኮር ሸለቆም የከብቶች ማረፊያ ይሆናል።

11“ነገር ግን እግዚአብሔርን ለተዋችሁት ለእናንተ፣

የተቀደሰ ተራራዬን ለረሳችሁት፣

‘ዕጣ ፈንታ’ ለተባለ ጣዖት ቦታ ላዘጋጃችሁት፣

‘ዕድል’ ለተባለም ጣዖት ድብልቅ የወይን ጠጅ በዋንጫ ለሞላችሁት፣

12ተጣርቼ ስላልመለሳችሁ፣

ተናግሬ ስላልሰማችሁ፣

በፊቴ ክፉ ነገር ስላደረጋችሁ፣

የሚያስከፋኝን ነገር ስለ መረጣችሁ፣

ለሰይፍ እዳርጋችኋለሁ፤

ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ።”

13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ባሮቼ ይበላሉ፤

እናንተ ግን ትራባላችሁ፤

ባሮቼ ይጠጣሉ፤

እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤

ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤

እናንተ ግን ታፍራላችሁ።

14ባሮቼ፣

ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ፤

እናንተ ግን፣

ልባችሁ በማዘኑ ትጮኻላችሁ፤

መንፈሳችሁ በመሰበሩም ወዮ ትላላችሁ።

15ስማችሁንም፣

የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤

ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤

ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል።

16ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በረከትን የሚጠራ፣

በእውነት አምላክ ስም ይባረካል፤

በምድሪቱ መሐላን የሚምል፣

በእውነት አምላክ ስም ይምላል፤

ያለፉት ችግሮች ተረስተዋል፤

ከዐይኖቼም ተሰውረዋል።

አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር

17“እነሆ፤ እኔ፣

አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤

ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤

አይታወሱም።

18ነገር ግን በምፈጥረው፣

ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ።

ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣

ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና።

19በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤

በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤

የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣

ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።

20“ከእንግዲህም በዚያ፣

ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሕይወት የሚኖር ሕፃን፣

ወይም ዕድሜ ያልጠገበ አረጋዊ አይኖርም፤

አንድ መቶ ዓመት የሞላው ሰው ቢሞት፣

በዐጭር እንደ ተቀጨ ይቈጠራል፤

አንድ ሰው መቶ ዓመት ሳይሞላው ቢሞት፣

እንደ ተቀሠፈ ይገመታል።

21ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤

ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።

22ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤

ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤

የሕዝቤ ዕድሜ፣

እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤

እኔ የመረጥኋቸው፣

በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።

23ድካማቸው በከንቱ አይቀርም፤

ዕድለ ቢስ ልጆችም አይወልዱም፤

እነርሱና ዘራቸው፣

እግዚአብሔር የባረከው ሕዝብ ይሆናሉ።

24ገና ሳይጣሩ እመልስላቸዋለሁ፤

ተናግረው ሳይጨርሱ እሰማለሁ።

25ተኵላና የበግ ጠቦት በአንድነት ይበላሉ፤

አንበሳ እንደ በሬ ሣር ይበላል፤

እባብ ትቢያ ይልሳል፤

በተቀደሰው ተራራዬም፣

ጕዳት አያደርሱም፤ ጥፋት አያመጡም፤”

ይላል እግዚአብሔር