ኢሳይያስ 4 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 4:1-6

1በዚያን ቀን ሰባት ሴቶች

አንዱን ወንድ ይዘው፣

“የራሳችንን ምግብ እንበላለን፤

የራሳችንንም ልብስ እንለብሳለን፤

በአንተ ስም ብቻ እንጠራና፣

ውርደታችንን አስቀርልን” ይሉታል።

የእግዚአብሔር ዛፍ ቅርንጫፍ

2በዚያን ቀን የእግዚአብሔር ዛፍ ቅርንጫፍ ያማረና የከበረ ይሆናል፤ የምድሪቱም ፍሬ ከጥፋት ለተረፈው የእስራኤል ወገን ኵራትና ክብር ይሆናል። 3በጽዮን የቀሩት፣ በኢየሩሳሌምም የተረፉት፣ በኢየሩሳሌም በሕይወት ከተመዘገቡት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ። 4ጌታ የጽዮንን ሴቶች እድፍ ያጥባል፤ ኢየሩሳሌምንም ከተነከረችበት ደም በፍርድና በሚያቃጥል መንፈስ4፥4 ወይም በእግዚአብሔር መንፈስ ማለት ነው። ያነጻታል። 5ከዚያም እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይና በዚያ በሚሰበሰቡትም ሁሉ ላይ በቀን ደመናንና ጢስን፣ በሌሊትም የሚንበለበለውን የእሳት ብርሃን ይፈጥራል፤ በክብሩ ሁሉ ላይ መጋረጃ ይሆናል፤ 6ከቀኑ ሙቀት ጥላና መከለያ፣ ከውሽንፍርና ከዝናብም መጠጊያና መሸሸጊያ ስፍራ ይሆናል።