ኢሳይያስ 30 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 30:1-33

ወዮ ለእንቢተኛ ሕዝብ

1“ለዐመፀኞች ልጆች ወዮላቸው”

ይላል እግዚአብሔር

“የእኔ ያልሆነውን ሐሳብ ይከተላሉ፤

ከመንፈሴ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤

በኀጢአት ላይ ኀጢአት ይጨምራሉ።

2እኔን ሳይጠይቁ፣

ወደ ግብፅ ይወርዳሉ፤

የፈርዖንን ከለላ፣

የግብፅንም ጥላ ለመጠጊያነት ይፈልጋሉ።

3ነገር ግን የፈርዖን ከለላ ውርደት ይሆንባችኋል፤

የግብፅም ጥላ ኀፍረት ያመጣባችኋል።

4ምንም እንኳ ሹሞች በጣኔዎስ ቢኖሯቸውም፣

መልእክተኞቻቸው ሓኔስ ቢደርሱም፣

5ውርደትና ኀፍረት ብቻ እንጂ

ርዳታም ሆነ ረብ በማያስገኙላቸው፣

ምንም ጥቅም በማይሰጧቸው ሰዎች ምክንያት

ሁሉም ለኀፍረት ይዳረጋሉ።”

6በኔጌቭ ስላሉት እንስሳት የተነገረ ንግር፤

መልእክተኞች ሀብታቸውን በአህያ፣

ውድ ዕቃዎቻቸውን በግመል ጭነው፣

ተባዕትና እንስት አንበሶች፣

መርዘኛና ተወርዋሪ እባቦች በሚኖሩበት፣

መከራና ጭንቅ ባለበት ምድር ዐልፈው፣

ወደማይጠቅማቸው ወደዚያ ሕዝብ፣

7ርዳታዋም ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ወደ ሆነው ወደ ግብፅ ይሄዳሉ።

ስለዚህ ስሟን፣

ረዓብ፣ ምንም የማትጠቅም ብዬ እጠራታለሁ።

8አሁንም ሂድ፤ በሰሌዳ ላይ ጻፍላቸው፤

በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ክተብላቸው፤

ለሚመጡትም ዘመናት፣

ለዘላለም ምስክር ይሆናል፤

9እነዚህም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለመስማት የማይፈልጉ፣

ዐመፀኛ ሕዝቦችና አታላይ ልጆች ናቸው።

10ባለ ራእዮችን፣

“ከእንግዲህ ራእይን አትዩ” ይላሉ፤

ነቢያትንም እንዲህ ይላሉ፤

“እውነተኛውን ትንቢት ከእንግዲህ አትንገሩን፤

ደስ የሚያሰኘውን ንገሩን፤

የሚያማልለውን ተንብዩልን።

11ከዚህ መንገድ ፈቀቅ በሉ፤

ከጐዳናውም ራቁ፤

ከእስራኤል ቅዱስ ጋር

ፊት ለፊት አታጋጥሙን።”

12ስለዚህ፣ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፤

“ይህን ቃል ስላቃለላችሁ፣

ግፍን ስለ ታመናችሁ፣

ማታለልን ስለ ተደገፋችሁ፣

13ስለዚህ ይህ ኀጢአት፣

ተሰነጣጥቆ ሊወድቅ እንደ ደረሰ፣

ሳይታሰብ ድንገት እንደሚወድቅ ረዥም ቅጥር ይሆንባችኋል።

14ከስብርባሪዎቹም መካከል፣

ለፍም መጫሪያ፣

ለውሃ መጥለቂያ ገል እስከማይገኝ ድረስ፣

ምንም ሳይቀር ክፉኛ እንደሚንኰታኰት፣

የሸክላ ዕቃ ይደቅቃል።”

15የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤

በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤

እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤

16ደግሞም ‘አይሆንም፣ በፈረስ እንሸሻለን’ አላችሁ፤

ስለዚህ ትሸሻላችሁ።

ደግሞም፣ ‘በፈጣን ፈረስ እናመልጣለን’ አላችሁ፤

ስለዚህ አሳዳጆቻችሁም ፈጣን ይሆናሉ።

17በተራራ ዐናት ላይ እንደ ተተከለ ሰንደቅ ዐላማ፣

በኰረብታም ላይ እንደ ቆመ ምልክት

ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ

በአንድ ሰው ዛቻ፣

ሺሕ ሰው ይሸሻል፤

በአምስት ሰው፣

ሁላችሁ ትሸሻላችሁ።”

18እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤

ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል።

እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣

እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት የተባረኩ ናቸው።

19በኢየሩሳሌም የምትኖሩ የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅሱም። ለርዳታ ወደ እርሱ ስትጮኹ እንዴት ምሕረት አያደርግላችሁ! ጩኸትህን እንደ ሰማም ፈጥኖ ይመልስልሃል። 20ጌታ የጭንቀት እንጀራና የመከራ ውሃ ቢሰጥህም፣ አስተማሪህ ከእንግዲህ አይሰወርብህም፤ ዐይኖችህም አስተማሪህን ያያሉ። 21ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዘወር ብትል ጆሮህ ከኋላህ፣ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል። 22ከዚያም በብር የተለበጡትን ጣዖቶችህንና በወርቅ የተለበዱ ምስሎችህን ታዋርዳለህ፤ “ከዚህ ወግዱ!” ብለህም እንደ መርገም ጨርቅ ትጥላቸዋለህ።

23በምድርም ለዘራኸው ዘር ዝናብን ይሰጥሃል፤ ከመሬትም የሚገኘው ፍሬ ምርጥና የተትረፈረፈ ይሆናል። በዚያን ቀን ከብቶችህ በትልቅ ሜዳ ላይ ይሰማራሉ። 24የዕርሻ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በላይዳ የተለየውን ገፈራና ድርቆሽ ይበላሉ። 25በታላቁ የዕልቂት ቀን ምሽጎች ሲፈርሱ፣ በረጅም ተራራ ሁሉና ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ላይ ወራጅ ወንዝ ይፈስሳል። 26እግዚአብሔር የሕዝቡን ስብራት ሲጠግን፣ ያቈሰለውንም ሲፈውስ፣ ጨረቃ እንደ ፀሓይ ታበራለች፤ የፀሓይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት ዕጥፍ ይደምቃል።

27እነሆ፤ የእግዚአብሔር ስም፣

ከሚነድድ ቍጣ፣ ጥቅጥቅ ካለና ከሚትጐለጐል የጢስ ደመና ጋር ከሩቅ ይመጣል፤

ከንፈሮቹ ቍጣን የተሞሉ ናቸው፤

ምላሱም የሚባላ እሳት ነው።

28እስትንፋሱ እንደሚጠራርግ፣

እስከ ዐንገት እንደሚደርስም የውሃ ሙላት ነው፤

መንግሥታትን በጥፋት ወንፊት ያበጥራቸዋል፤

በሕዝቦችም መንጋጋ፣

መንገድ የሚያስት ልጓም ያስገባል።

29በሌሊት የተቀደሰ በዓል ስታከብሩ

እንደምትዘምሩ፣

ትዘምራላችሁ፤

ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣

ወደ እስራኤል ዐለት፣

ሰዎች ዋሽንት እየነፉ በደስታ እንደሚወጡ፣

የእናንተም ልብ እንዲሁ ሐሤት ያደርጋል።

30እግዚአብሔር በሚነድድ ቍጣና በሚባላ እሳት፣

በወጀብና በነጐድጓድ፣ በበረዶም ድንጋይ፣

ግርማ የተሞላበትን ድምፁን ሰዎች እንዲሰሙ አድርጎ ያሰማል፤

ክንዱም ስትወርድ ያሳያቸዋል።

31የእግዚአብሔር ድምፅ አሦርን ያስደነግጣል፤

በትሩም ይመታቸዋል።

32እግዚአብሔር የሚያወርድባቸው የቅጣት

በትር ሁሉ፣

በከበሮና በበገና ድምፅ የታጀበ ነው፤

በጦርነትም ክንዱን አሳይቶ መታቸው።

33ከቀድሞ ጀምሮ ቶፌት የተባለ የማቃጠያ

ስፍራ ተዘጋጅቷል፤

ለንጉሡም ተበጅቷል፤

ማንደጃ ጕድጓዱም ሰፊና ጥልቅ ነው፤

በውስጡም ብዙ እሳትና ማገዶ አለ፤

የእግዚአብሔርም እስትንፋስ

እንደ ፈሳሽ ድኝ ያቀጣጥለዋል።