ነህምያ 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ነህምያ 11:1-36

አዲሶቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች

11፥3-19 ተጓ ምብ – 1ዜና 9፥1-17

1በዚህ ጊዜ የሕዝቡ መሪዎች መኖሪያቸውን በኢየሩሳሌም አደረጉ፤ ከቀረው ሕዝብ ከዐሥር አንዱ እጅ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም፣ የቀሩት ዘጠኙ እጅ ደግሞ በየራሳቸው ከተሞች እንዲኖሩ ዕጣ ተጣጣሉ። 2ሕዝቡም በኢየሩሳሌም ለመኖር በራሳቸው ፈቃድ የተነሣሡትን ሰዎች ሁሉ አመሰገኑ።

3እንግዲህ በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የአውራጃዪቱ መሪዎች እነዚህ ናቸው፤ በዚህ ጊዜም በይሁዳ ከተሞች የሚኖሩ የተወሰኑ እስራኤላውያን፣ ካህናት፣ ሌዋውያን፣ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና የሰሎሞን አገልጋዮች ዘሮች እያንዳንዳቸው በተለያዩ ከተሞች ባለ በየራሳቸው ንብረት ላይ ተቀመጡ፤ 4ከይሁዳና ከብንያም ወገን የሆኑት የተቀሩት ሰዎች ደግሞ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፤

ከይሁዳ ዘሮች፦

ከፋሬስ ዘር የመላልኤል ልጅ፣ የሰፋጥያስ ልጅ፣ የአማርያ ልጅ፣ የዘካርያስ ልጅ፣ የዖዝያ ልጅ አታያ፤

5ከሴሎ ዘር የዘካርያስ ልጅ፣ የዮያሪብ ልጅ፣ የዓዳያ ልጅ፣ የፆዛያ ልጅ፣ የኮልሖዜ ልጅ፣ የባሮክ ልጅ መዕሤያ።

6በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የፋሬስ ዘሮች በጠቅላላ 468 ብርቱ ሰዎች ናቸው።

7ከብንያም ዘሮች፦

የየሻያ ልጅ፣ የኢቲኤል ልጅ፣ የመዕሤያ ልጅ፣ የቆላያ ልጅ፣ የፈዳያ ልጅ፣ የዮእድ ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ ሰሉ፤ 8ተከታዮቹም ጌቤና ሳላይ 928 ወንዶች፤

9የእነዚህም አለቃ የዝክሪ ልጅ ኢዩኤል ሲሆን፣ የሐስኑአ ልጅ ይሁዳ የከተማዪቱ “ሁለተኛ አውራጃ” የበላይ ነበር።

10ከካህናቱ፦

የዮያሪብ ልጅ ዮዳኤ፤ ያኪን፤

11የእግዚአብሔር ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የሜሱላም ልጅ፣ የኪልቅያስ ልጅ ሠራያ፤ 12የቤተ መቅደሱን ሥራ ያከናወኑት ወንድሞቻቸው፣ 822 ሰዎች፤

የመልክያ ልጅ፣ የፋስኮር ልጅ፣ የዘካርያስ ልጅ፣ የአማሲ ልጅ፣ የፈላልያ ልጅ፣ የይሮሐም ልጅ ዓዳያ፤ 13ወንድሞቹ የሆኑት የየቤተ ሰቡ አለቆች 242 ወንዶች፤

የኢሜር ልጅ የምሺሌሞት ልጅ፣ የአሕዛይ ልጅ፣ የኤዝርኤል ልጅ አማስያ፤ 14እንዲሁም ብርቱ የሆኑት ወንድሞቹ11፥14 አብዛኞቹ የሰብዓ ሊቃናት ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ወንድሞቻቸው ይላል። 128 ሰዎች፤

የእነርሱም ዋና አለቃ የሐግዶሊም ልጅ ዘብድኤል ነበር።

15ከሌዋውያኑ፦

የቡኒ ልጅ፣ የአሳብያ ልጅ፣ የዓዝሪቃም ልጅ፣ የአሱብ ልጅ ሻማያ፤

16እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት የውጩ ሥራ ኀላፊዎች የነበሩት፣ ከሌዋውያን አለቆች ሁለቱ ሳባታይና ዮዛባት።

17በምስጋናና በጸሎት ጊዜ ይመራ የነበረው የዋናው አለቃ የአሳፍ ልጅ፣ የዘብዲ ልጅ፣ የሚካ ልጅ መታንያ፣ ከወንድሞቹ ሁለተኛ የሆነው በቅበቃር፣ የኤዶታም ልጅ፣ የጋላል ልጅ፣ የሳሙስ ልጅ አብድያ።

18በቅድስቲቱ ከተማ ውስጥ የነበሩት የሌዋውያኑ ቍጥር 284 ነበረ።

19በር ጠባቂዎች፦

ዓቁብ፣ ጤልሞንና በሮቹን የሚጠብቁ ወንድሞቻቸው፣ 172 ሰዎች።

20የቀሩት እስራኤላውያንም ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በይሁዳ ከተሞች ሁሉ በየርስታቸው ተቀመጡ።

21የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች በዖፌል ኰረብታ ላይ ተቀመጡ፤ ሲሐና ጊሽጳ በእነርሱ ላይ ያዙ ነበር።

22በኢየሩሳሌም የሌዋውያኑ ዋና አለቃ የሚካ ልጅ፣ የመታንያ ልጅ፣ የሐሻብያ ልጅ፣ የባኒ ልጅ ኦዚ ነበረ፤ ኦዚ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ለሚዘመረው መዝሙር ኀላፊ ከነበሩት ከአሳፍ ዘሮች አንዱ ነበረ። 23መዘምራኑ የየዕለቱን ተግባራቸውን በሚቈጣጠረው በንጉሡ ትእዛዝ ሥር ነበሩ።

24የይሁዳ ልጅ የዛራ ዘር የሆነው የሜሴዜቤል ልጅ ፈታያ ሕዝቡን በሚመለከት ጕዳይ ሁሉ የንጉሡ ተወካይ ነበር።

25ከይሁዳ ሕዝብ ጥቂቱ በመንደሮችና በዕርሻ ቦታዎች፣ በቂርያት አርባቅና በዙሪያዋ ባሉ መኖሪያዎቿ፣ በዲቦንና በመኖሪያዎቿ፣ በይቀብጽኤልና በመንደሮቿ ተቀመጡ፤ 26በኢያሱ፣ በሞላዳ፣ በቤትጳሌጥ፣ 27በሐጸርሹዓል፣ በቤርሳቤህና በመኖሪያዎቿ፣ 28በጺቅላግ፣ በምኮናና በመኖሪያዎቿ፣ 29በዓይንሪሞን፣ በጾርዓ፣ በየርሙት፣ 30በዛኖዋ፣ በዓዶላምና በመንደሮቻቸው፣ በለኪሶና በዕርሻዎቿ፣ በዓዜቃና በመንደሮቿ። ስለዚህ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ሄኖም ሸለቆ ባለው ስፍራ ሁሉ ተቀመጡ። 31ከጌባ የመጡት የብንያም ዘሮች በማክማስ፣ በጋያ፣ በቤቴልና በመኖሪያዎቿ፣ 32በዓናቶት፣ በኖብና በሐናንያ፣ 33በሐጾር፣ በራማና በጊቴም፣ 34በሐዲድ፣ በስቦይምና በንበላት፣ 35በሎድና በኦኖ፣ ደግሞም “ጌሃርሻም”11፥35 ትርጓሜው “የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ሸለቆ” በተባለው ስፍራ ተቀመጡ።

36በይሁዳ ከነበሩት ሌዋውያን ከፊሎቹ በብንያም ምድር ተቀመጡ።