ቈላስይስ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ቈላስይስ 2:1-23

1ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ስለማያውቁ ሁሉ ምን ያህል እየተጋደልሁ እንደ ሆነ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ 2ደግሞም ልባቸው እንዲጽናናና በፍቅር እንዲተሳሰሩ፣ ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጽግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ፤ 3የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በእርሱ ዘንድ ነውና። 4ማንም ንግግር በማሳመር እንዳያታልላችሁ ይህን እነግራችኋለሁ። 5ምንም በሥጋ ከእናንተ ርቄ ብገኝ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና በሥርዐት መኖራችሁንና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።

ከሰው ሠራሽ ሥርዐት በክርስቶስ ነጻ መሆን

6እንግዲህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት እንዲሁ በእርሱ ኑሩ፤ 7በእርሱ ተተክላችሁና ታንጻችሁ እንደ ተማራችሁት በእምነት ጸንታችሁ፣ የተትረፈረፈ ምስጋና እያቀረባችሁ ኑሩ።

8በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።

9የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል በእርሱ ይኖራልና፤ 10እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል። 11በእርሱ ሆናችሁ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ ተገረዛችሁ፤ በክርስቶስም መገረዝ የሥጋን ኀጢአታዊ ባሕርይ አስወገዳችሁ፤ 12በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፣ እርሱን ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ኀይል በማመን ከእርሱ ጋር ደግሞ ተነሣችሁ።

13እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለ መገረዝ ሙታን ሳላችሁ፣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ2፥13 አንዳንድ የጥንት ቅጆች አደረገን ይላሉ።፤ ኀጢአታችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤ 14ሲቃወመንና ሲጻረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። 15የአለቆችንና የባለሥልጣናትንም ማዕረግ በመግፈፍ በመስቀሉ2፥15 ወይም በእርሱ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ።

16እንግዲህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ ወር መባቻንና ሰንበትን በማክበር ነገር ማንም አይፍረድባችሁ፤ 17እነዚህ ሊመጡ ላሉ ነገሮች ጥላ ናቸውና፤ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። 18ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ 19ይህ ሰው፣ አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ እየተጋጠመ ምግብንም እየተቀበለ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ከሚያድግበት ራስ ከሆነው ጋር ግንኙነት የለውም።

20ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ ታዲያ ለምን እንደዚህ ዓለም ሰው ለሕጎቹ ተገዥ ትሆናላችሁ? 21“አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ 22እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። 23እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።