ምሳሌ 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 7:1-27

ከአመንዝራ ሴት መራቅ

1ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ጠብቅ፤

ትእዛዜንም በውስጥህ አኑር።

2ትእዛዜን ጠብቅ፤ በሕይወት ትኖራለህ፤

ትምህርቴንም እንደ ዐይንህ ብሌን ተንከባከበው።

3በጣትህ ላይ እሰረው፤

በልብህ ጽላት ላይ ጻፈው።

4ጥበብን፣ “እኅቴ ነሽ” በላት፤

ማስተዋልንም፣ “ዘመዴ ነህ” በለው፤

5ከአመንዝራ ሴት፣

በአንደበቷም ከምታታልል ዘልዛላ ሴት ይጠብቁሃል።

6በቤቴ መስኮት፣

በዐይነ ርግቡ ወደ ውጭ ተመለከትሁ።

7ማስተዋል የጐደለውን ወጣት፣

ብስለት ከሌላቸው መካከል አየሁት፤

ከጕልማሶችም መካከል ለየሁት።

8የቤቷን አቅጣጫ ይዞ፣

በቤቷ ማእዘን አጠገብ ባለው መንገድ ያልፍ ነበር፤

9ቀኑ መሸትሸት ሲል፣

በውድቅት ሌሊት፣ በጽኑ ጨለማ።

10ከዚያም አንዲት ሴት ልታገኘው ወጣች፤

እንደ ዝሙት ዐዳሪ ለብሳ፣ ለማሳሳት ታጥቃ።

11ጯኺና ማን አለብኝ ባይ ናት፤

እግሮቿ ዐርፈው ቤት አይቀመጡም፤

12አንዴ በመንገድ፣ አንዴ በአደባባይ፣

በየማእዘኑም ታደባለች።

13አፈፍ አድርጋ ይዛ ሳመችው፤

ኀፍረቷንም ጥላ እንዲህ አለችው፤

14“በቤቴ የኅብረት መሥዋዕት7፥14 በተለምዶ የሰላም መሥዋዕት ይባላል። ማቅረብ ነበረብኝ፤

ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ፤

15ስለዚህ አንተን ለማግኘት ወጣሁ፤

ፈልጌህ ነበር፤ ይኸው አገኘሁህ።

16ዐልጋዬን ከግብፅ የመጣ፣

ጌጠኛ በፍታ አልብሼዋለሁ።

17ዐልጋዬን፣

የከርቤ፣ የዓልሙንና የቀረፋ ሽቱ አርከፍክፌበታለሁ።

18ና፤ እስኪነጋ በጥልቅ ፍቅር እንርካ፤

በፍቅር ራሳችንን እናስደስት።

19ባሌ እቤት የለም፤

ሩቅ አገር ሄዷል።

20በገንዘብ የተሞላ ቦርሳ ወስዷል፤

ጨረቃዋ ሙሉ እስክትሆን አይመለስም።”

21በሚያግባቡ ቃላት አሳተችው፤

በለሰለሰ አንደበቷ አታለለችው።

22ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ፣

ወደ ወጥመድ7፥22 የሱርሰት (የሰብዓ ሊቃናትም) ትርጕም እና ዕብራይስጡ ተላላ ይላሉ። እንደሚገባ አጋዘን፣7፥22 የዚህ ስንኝ የዕብራይስጡ ትርጓሜ በርግጠኝነት አይታወቅም።

ሳያንገራግር ተከተላት፤

23ፍላጻ ጕበቱን እስኪወጋው ድረስ፣

ሕይወቱን እንደሚያሳጣው ሳያውቅ፣

በርራ ወደ ወጥመድ እንደምትገባ ወፍ ሆነ።

24ልጆቼ ሆይ፤ አሁንም አድምጡኝ፤

የምለውንም ልብ ብላችሁ ስሙኝ።

25ልባችሁን ወደ መንገዷ አታዘንብሉ፤

ወደ ስሕተት ጐዳናዋም አትግቡ።

26አዋርዳ የጣለቻቸው ብዙ ናቸው፤

የገደለቻቸውም ስፍር ቍጥር የላቸውም።

27ቤቷ ወደ ሲኦል7፥27 ወይም መቃብር የሚወስድ፣

ወደ ሞት ማደሪያም የሚያወርድ ጐዳና ነው።