ምሳሌ 18 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 18:1-24

1ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤

ቅን የሆነውንም ፍርድ ሁሉ ይቃወማል።

2ተላላ ከማስተዋል ርካታን አያገኝም፤

የራሱን ሐሳብ በመግለጥ ግን ደስ ይለዋል።

3ክፋት ስትመጣ ንቀት ትከተላለች፤

ከዕፍረትም ጋር ውርደት ትመጣለች።

4ከሰው አፍ የሚወጡ ቃላት ጥልቅ ውሆች ናቸው፤

የጥበብም ምንጭ እንደሚንዶለዶል ፏፏቴ ነው።

5ለክፉ ሰው ማድላት፣

ንጹሑንም ፍትሕ መንሣት ተገቢ አይደለም።

6የተላላ ከንፈር ጠብ ያመጣበታል፤

አፉም በትር ይጋብዛል።

7ተላላ ሰው አፉ መጥፊያው ነው፤

ከንፈሮቹም ለነፍሱ ወጥመድ ናቸው።

8የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤

ወደ ሰው ውስጣዊ ክፍል ዘልቆ ይገባል።

9ለሥራው ደንታ የሌለው ሰው፣

የአጥፊ ወንድም ነው።

10የእግዚአብሔር ስም ጽኑ ግንብ ነው፤

ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል።

11የባለጠጎች ሀብት የተመሸገ ከተማቸው ነው፤

እንደማይወጣ ረዥም ግንብም ይቈጥሩታል።

12ከውድቀቱ በፊት ሰው ልቡ ይታበያል፤

ትሕትና ግን ክብርን ትቀድማለች።

13ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣

ቂልነትና ዕፍረት ይሆንበታል።

14በሕመም ጊዜ፣ ሰውን መንፈሱ ትደግፈዋለች፤

የተሰበረውን መንፈስ ግን ማን ሊሸከም ይችላል?

15የአስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይገበያል፤

የጠቢብም ጆሮ አጥብቆ ይሻታል።

16እጅ መንሻ ለሰጪው መንገድ ትከፍትለታለች፤

ታላላቅ ሰዎች ፊትም ታቀርበዋለች።

17አስቀድሞ ጕዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤

ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው።

18ዕጣ መጣጣል ሙግትን ያስቆማል፤

ኀይለኛ ባላንጣዎችንም ይገላግላል።

19የተበደለ ወንድም ከተመሸገ ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤

ጠቡም እንደ ጠንካራ የግንብ መዝጊያ ነው።

20ሰው በአንደበቱ ፍሬ ሆዱ ይጠግባል፤

በከንፈሩም ምርት ይረካል።

21አንደበት የሞትና የሕይወት ኀይል አላት፤

የሚወድዷትም ፍሬዋን ይበላሉ።

22ሚስት የሚያገኝ መልካም ነገርን ያገኛል፤

ከእግዚአብሔርም ዘንድ ሞገስን ይቀበላል።

23ድኻ በመለማመጥ ምሕረት ይለምናል፤

ሀብታም ግን በማናለብኝነት ይመልሳል።

24ወዳጅ የሚያበዛ ሰው ራሱን ለጥፋት ይዳርጋል፤

ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ።