ምሳሌ 17 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 17:1-28

1ጠብ እያለ ግብዣ17፥1 ዕብራይስጡ መሥዋዕት ይላል። ከሞላበት ቤት ይልቅ፣

በሰላምና በጸጥታ የእንጀራ ድርቆሽ ይሻላል።

2ጠቢብ አገልጋይ በወራዳ ልጅ ላይ ሥልጣን ይኖረዋል፤

ከወንድማማቾቹም እንደ አንዱ ውርስ ይካፈላል።

3ማቅለጫ ለብር፣ ከውር ለወርቅ ነው፤

እግዚአብሔር ግን ልብን ይመረምራል።

4እኩይ ሰው ክፉ ንግግር ያዳምጣል፤

ሐሰተኛም የተንኰለኛን አንደበት በጥንቃቄ ይሰማል።

5በድኾች የሚያፌዝ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤

በሌላው ሰው መከራ ደስ የሚለው ከቅጣት አያመልጥም።

6የልጅ ልጆች ለአረጋውያን ዘውድ ናቸው፤

ወላጆችም ለልጆቻቸው አለኝታ ናቸው።

7መልካም አነጋገር17፥7 ወይም የኵራት አነጋገር ለተላላ አይሰምርለትም፤

ለገዥማ ሐሰተኛ አንደበት የቱን ያህል የከፋ ይሆን!

8እጅ መንሻ ለሰጭው እንደ ድግምት ዕቃ ነው፤

በሄደበትም ቦታ ሁሉ ይሳካለታል።

9በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ያዳብራል፤

ነገርን የሚደጋግም ግን የልብ ወዳጆችን ይለያያል።

10መቶ ግርፋት ተላላን ከሚሰማው ይልቅ፣

ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል።

11ክፉ ሰው ዐመፅን ብቻ ይፈልጋል፤

በእርሱም ላይ ጨካኝ መልእክተኛ ይላክበታል።

12ተላላን በቂልነቱ ከመገናኘት፣

ግልገሎቿን የተነጠቀችን ድብ መጋፈጥ ይሻላል።

13በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልስ ሰው፣

ክፉ ነገር ከቤቱ አይርቅም።

14ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤

ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ።

15በደለኛውን ንጹሕ ማድረግ ሆነ፣ ንጹሑን በደለኛ ማድረግ፣

ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸው።

16ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣

ተላላ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው?

17ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤

ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።

18ማስተዋል የጐደለው ሰው ቃል በመግባት እጅ ይመታል፤

ለወዳጁም ዋስ ይሆናል።

19ጠብ የሚወድድ ኀጢአትን ይወድዳል፤

በሩን ከፍ አድርጎ የሚሠራም ጥፋትን ይጋብዛል።

20ጠማማ ልብ ያለው ሰው አይሳካለትም፤

በአንደበቱ የሚቀላምድም መከራ ላይ ይወድቃል።

21ተላላ ልጅ መውለድ ሐዘን ያስከትላል፤

የተላላም አባት ደስታ የለውም።

22ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤

የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል።

23ክፉ ሰው ፍትሕ ለማዛባት፣

በስውር ጕቦ ይቀበላል።

24አስተዋይ ሰው ጥበብን ከፊቱ አይለያትም፤

የተላሎች ዐይኖች ግን እስከ ምድር ዳርቻ ይንከራተታሉ።

25ተላላ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤

ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል።

26ንጹሑን ሰው መቅጣት ተገቢ አይደለም፤

ሹሞችን ስለ ቅንነታቸው መግረፍ መልካም አይደለም።

27ዐዋቂ ሰው ንግግሩ ቍጥብ ነው፤

አስተዋይም መንፈሱ የረጋ ነው።

28አላዋቂ እንኳ ዝም ቢል ጠቢብ፣

አንደበቱንም ቢገዛ አስተዋይ ይመስላል።