ምሳሌ 15 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 15:1-33

1የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤

ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል።

2የጠቢብ አንደበት ዕውቀትን ታወድሳለች፤

የተላሎች አንደበት ግን ቂልነትን ያፈልቃል።

3የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤

ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ።

4ፈውስ የምታመጣ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት፤

አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ትሰብራለች።

5ተላላ የአባቱን ምክር ይንቃል፤

መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል።

6የጻድቃን ቤት በብዙ ሀብት የተሞላ ነው፤

የክፉዎች ገቢ ግን መከራን ታመጣባቸዋለች።

7የጠቢባን ከንፈር ዕውቀትን ታስፋፋለች፤

የተላሎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።

8እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤

የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል።

9እግዚአብሔር የክፉዎችን መንገድ ይጸየፋል፤

ጽድቅን የሚከታተሉትን ግን ይወድዳቸዋል።

10ከመንገድ የሚወጣ ሰው ጥብቅ ቅጣት ይጠብቀዋል፤

ዕርምትን የሚጠላ ይሞታል።

11ሲኦልና የሙታን ዓለም15፥11 በዕብራይስጡ ሲኦልና አባዶን ይላል። በእግዚአብሔር ፊት የተገለጡ ናቸው፤

የሰዎች ልብማ የቱን ያህል የታወቀ ነው!

12ፌዘኛ መታረምን ይጠላል፤

ጠቢባንንም አያማክርም።

13ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፤

የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል።

14አስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይሻል፤

የተላላ አፍ ግን ቂልነትን ያመነዥካል።

15የተጨቈኑ ሰዎች ዘመናቸው ሁሉ የከፋ ነው፤

በደስታ የተሞላ ልብ ግን የማይቋረጥ ፈንጠዝያ አለው።

16እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር፣

ሁከት ካለበት ትልቅ ሀብት ይበልጣል።

17ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣

ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል።

18ግልፍተኛ ሰው ጠብ ያነሣሣል፤

ታጋሽ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል።

19የሀኬተኛ መንገድ በእሾኽ የታጠረች ናት፤

የቅኖች መንገድ ግን የተጠረገ አውራ ጐዳና ነው።

20ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤

ተላላ ሰው ግን እናቱን ይንቃል።

21ማመዛዘን የጐደለው ሰው ቂልነት ያስደስተዋል፤

አስተዋይ ሰው ግን ቀጥተኛውን መንገድ ይከተላል።

22ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤

በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።

23ሰው ተገቢ መልስ በመስጠት ደስታን ያገኛል፤

በወቅቱም የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!

24ወደ ሲኦል15፥24 ወይም መቃብር ከመውረድ እንዲድን፣

የሕይወት መንገድ ጠቢቡን ሰው ወደ ላይ ትመራዋለች።

25እግዚአብሔር የትዕቢተኛውን ቤት ያፈርሰዋል፤

የመበለቲቱን ዳር ድንበር ግን እንዳይደፈር ይጠብቃል።

26እግዚአብሔር የክፉውን ሰው ሐሳብ ይጸየፋል፤

የንጹሓን ሐሳብ ግን ደስ ያሰኘዋል።

27ስስታም ሰው በቤተ ሰቡ ላይ ችግር ያመጣል፤

ጕቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።

28የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል፤

የክፉ ሰው አፍ ግን ክፋትን ያጐርፋል።

29እግዚአብሔር ከክፉዎች ሩቅ ነው፤

የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።

30ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል፤

መልካም ዜናም ዐጥንትን ያለመልማል።

31ሕይወት ሰጭ የሆነውን ተግሣጽ የሚሰማ፣

በጠቢባን መካከል ይኖራል።

32ተግሣጽን የሚንቅ ራሱን ይንቃል፤

ዕርምትን የሚቀበል ግን ማስተዋልን ያገኛል።

33እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብን መማር ነው፤15፥33 ወይም ጥበብ እግዚአብሔርን መፍራት ታስተምራለች።

ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች።