ማቴዎስ 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማቴዎስ 11:1-30

መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የላከው ጥያቄ

11፥2-19 ተጓ ምብ – ሉቃ 7፥18-35

1ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ፣ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች11፥1 ግሪኩ ወደ ከተሞቻቸው ይላል። ሄደ።

2ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣ 3“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።

4ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ 5ዕውሮች ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች11፥5 የግሪኩ ቃል የግድ ከለምጽ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን፣ የተለያዩ የቈዳ በሽታዎችንም ያመለክታል። ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤ 6በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”

7የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸንበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ? 8ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ። 9ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው። 10እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤

“ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣

ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’

11እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው፤ 13ነቢያትም፣ የሙሴ ሕግም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና። 14እንግዲህ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እርሱ ነው። 15ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።

16“ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤

17“ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤

አልጨፈራችሁም፤

ሙሾ አወረድንላችሁ፤

አላለቀሳችሁም’

18ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና። 19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ፣ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች።”

ንስሓ ስላልገቡ ከተሞች የተነገረ ወዮታ

11፥21-23 ተጓ ምብ – ሉቃ 10፥13-15

20ከዚያም ኢየሱስ ብዙውን ታምራት ያደረገባቸው ከተሞች ንስሓ ባለ መግባታቸው እንዲህ ሲል ወቀሳቸው፤ 21“ወዮልሽ ኮራዚን፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። 22ስለዚህ እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። 23አንቺም ቅፍርናሆም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ማለት ፈለግሽ? ነገር ግን ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ታምራት በሰዶም ቢደረግ ኖሮ፣ እስከ ዛሬ በቈየች ነበር። 24ስለዚህ እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ቅጣቱ ለሰዶም ይቀልላታል።”

ክርስቶስ የሚሰጠው ዕረፍት

11፥25-27 ተጓ ምብ – ሉቃ 10፥21-22

25በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ 26አዎን አባት ሆይ፤ ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድህ ሆኖ ተገኝቷልና።

27“ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።

28“እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። 29ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ 30ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”