ማርቆስ 4 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 4:1-41

የዘሪው ምሳሌ

4፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥1-15ሉቃ 8፥4-10

4፥13-20 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥18-23ሉቃ 8፥11-15

1በሌላ ጊዜ ደግሞ በባሕሩ አጠገብ ያስተምር ጀመር። እርሱ ባለበት አካባቢ እጅግ ብዙ ሕዝብ ስለ ተሰበሰበ፣ በባሕሩ ላይ ወዳለች ጀልባ ገብቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ባለው ስፍራ ላይ ተሰብስቦ ነበር። 2እርሱም ብዙ ነገሮችን በምሳሌ አስተማራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ 3“ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4ዘሩን በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5ሌላው በቂ ዐፈር በሌለበት በጭንጫ ቦታ ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። 7ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። 8ሌላው ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስድሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።”

9ቀጥሎም ኢየሱስ፣ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።

10ብቻውን በሆነ ጊዜ፣ ዐሥራ ሁለቱና አብረውት የነበሩት ሌሎች ስለ ምሳሌዎቹ ጠየቁት። 11እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ 12ይኸውም፣

“ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣

መስማቱን እንዲሰሙ

ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው

እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።”

13ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? 14ዘሪው ቃሉን ይዘራል። 15አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። 16እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ ቦታ ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ 17ነገር ግን ሥር የሌላቸው ስለ ሆኑ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። 18ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ 19ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። 20ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

የመቅረዙ መብራት ምሳሌ

21እንዲህም አላቸው፤ “መብራት አምጥታችሁ ከዕንቅብ ወይም ከዐልጋ ሥር ታስቀምጣላችሁን? የምታስቀምጡት በመቅረዙ ላይ አይደለምን? 22ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤ 23ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”

24በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። 25ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው።

የአዳጊው ዘር ምሳሌ

26ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። 27ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ 28ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ 29ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።”

የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ

4፥30-32 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥3132ሉቃ 13፥1819

30ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? 31በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ 32ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።”

33ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። 34ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።

ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ

4፥35-41 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥1823-27ሉቃ 8፥22-25

35ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው። 36እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ። 37በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። 38ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተ ኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስናልቅ አይገድህምን?” አሉት።

39እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ “ጸጥ፣ ረጭ በል!” አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ።

40ደቀ መዛሙርቱንም፣ “ስለ ምን እንዲህ ፈራችሁ? እስከዚህ እምነት የላችሁምን?” አላቸው።

41እነርሱም በፍርሀት ተውጠው እርስ በርሳቸው፣ “ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።