ማሕልየ መሓልይ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማሕልየ መሓልይ 2:1-17

ሙሽራዪቱ

1እኔ የሳሮን ጽጌረዳ፣

የሸለቆም አበባ2፥1 ጸደይ ከመሆኑ ቀደም ብሎ የሚበቅል ቢጫ፣ ሐምራዊና ነጭ ቀለም ያሉት የአበባ ተክል ዝርያ ሊሆን ይችላል። ነኝ።

ሙሽራው

2በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ፣

ውዴም በቈነጃጅት መካከል እንዲሁ ናት።

ሙሽራዪቱ

3በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ እንኮይ፣

ውዴም በጕልማሶች መካከል እንዲሁ ነው፤

በጥላው ሥር መቀመጥ ደስ ያሰኛል፤

የፍሬውም ጣፋጭነት ያረካኛል።

4ወደ ግብዣው አዳራሽ ወሰደኝ፤

በእኔ ላይ ያለው ዐላማው ፍቅር ነው።

5በዘቢብ አበረታቱኝ፤

በእንኮይም አስደስቱኝ፤

በፍቅሩ ተይዤ ታምሜአለሁና።

6ግራ እጁን ተንተርሻለሁ፤

ቀኝ እጁም ዐቅፎኛል።

7እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፣

ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣

ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት፣

በሚዳቋና በሜዳ ዋሊያ አማጥናችኋለሁ።

8እነሆ፤ የውዴ ድምፅ

በተራሮች ላይ እየዘለለ፣

በኰረብቶችም ላይ እየተወረወረ፣

ሲመጣ ይሰማኛል።

9ውዴ ሚዳቋ ወይም የዋሊያ ግልገል ይመስላል፤

እነሆ፤ ከቤታችን ግድግዳ ኋላ ቆሟል፤

በመስኮት ትክ ብሎ ወደ ውስጥ ያያል፤

በፍርግርጉም እያሾለከ ይመለከታል።

10ውዴም እንዲህ አለኝ፤

“ፍቅሬ ሆይ፤ ተነሺ፤

አንቺ የእኔ ቈንጆ፤ ከእኔ ጋር ነዪ።

11እነሆ! ክረምቱ ዐለፈ፤

ዝናቡም አባርቶ አበቃ፤

12አበቦች በምድር ላይ ታዩ፤

የዝማሬ ወቅት መጥቷል፤

የርግቦችም ድምፅ፣

በምድራችን ተሰማ።

13በለስ ፍሬዋን አፈራች፤

ያበቡ ወይኖችም መዐዛቸውን ሰጡ፤

ፍቅሬ ሆይ፤ ተነሺና ነዪ፤

አንቺ የእኔ ቈንጆ፤ ከእኔ ጋር ነዪ።”

ሙሽራው

14አንቺ በገደል ዐለት ንቃቃት፣

በተራሮችም ባሉ መደበቂያ ስፍራዎች ውስጥ ያለሽ ርግቤ ሆይ!

ፊትሽን አሳዪኝ፤

ድምፅሽንም አሰሚኝ፤

ድምፅሽ ጣፋጭ፣

መልክሽም ውብ ነውና።

15የወይን ተክሉን ቦታ፣

በማበብ ላይ ያለውን የወይን ተክል ቦታችንን፣

የሚያጠፉትን ቀበሮዎች፣

እነዚያን ትንንሽ ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን።

ሙሽራዪቱ

16ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ፣

እርሱ መንጋውን በውብ አበቦች መካከል ያሰማራል።

17ጎሕ ከመቅደዱ በፊት፣

ጥላውም ሳይሸሽ፣

ውዴ ሆይ፤ ተመለስ፤

ሚዳቋን ምሰል፤

ወይም በወጣ ገባ ኰረብቶች2፥17 ወይም የቤጠር ኰረብቶች

እንዳለው የዋሊያ ግልገል ሁን።