መዝሙር 97 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 97:1-12

መዝሙር 97

የእግዚአብሔር ድል አድራጊነት

1እግዚአብሔር ነገሠ፤ ምድር ደስ ይበላት፤

በሩቅ ያሉ የባሕር ጠረፎች ሐሤት ያድርጉ።

2ደመናና ጥቅጥቅ ያለ ጭጋግ በዙሪያው አለ፤

ጽድቅና ፍትሕ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።

3እሳት በፊቱ ይሄዳል፤

በዙሪያው ያሉትንም ጠላቶቹን ይፈጃል።

4መብረቁ ዓለምን አበራ፤

ምድርም አይታ ተንቀጠቀጠች።

5ተራሮች በእግዚአብሔር ፊት፣

በምድርም ሁሉ ጌታ ፊት እንደ ሰም ቀለጡ።

6ሰማያት ጽድቁን ያውጃሉ፤

ሕዝቦችም ሁሉ ክብሩን ያያሉ።

7ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ፣

በጣዖታትም የሚመኩ ሁሉ ይፈሩ፤

እናንተ አማልክት ሁሉ፤ ለእርሱ ስገዱ።

8እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ፍርድህ፣

ጽዮን ሰምታ ደስ አላት፤

የይሁዳም ሴት ልጆች ሐሤት አደረጉ።

9እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል ነህና፤

ከአማልክትም ሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ያልህ ነህ።

10እግዚአብሔርን የምትወድዱ ክፋትን ጥሉ፤

እርሱ የታማኞቹን ነፍስ ይጠብቃልና፤

ከዐመፀኞችም እጅ ይታደጋቸዋል።

11ብርሃን ለጻድቃን፣

ሐሤትም ልባቸው ለቀና ወጣ።

12እናንት ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤

ቅዱስ ስሙንም አመስግኑ።