መዝሙር 86 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 86:1-17

መዝሙር 86

የመከራ ጊዜ ጸሎት

የዳዊት ጸሎት።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን ወደ እኔ ጣል፤ ስማኝም፤

እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝና።

2ለአንተ የተለየሁ ሰው ነኝና ነፍሴን ጠብቃት፤

አንተ አምላኬ ሆይ፤

በአንተ የታመነብህን ባሪያህን አድን።

3ጌታ ሆይ፤ ማረኝ፤

ቀኑን ሙሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና።

4የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፤

ጌታ ሆይ፤ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።

5ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ፤

ለሚጠሩህ ሁሉ ምሕረትህ ወሰን የለውም።

6እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን አድምጥ፤

የልመናዬን ጩኸት ስማ።

7አንተ ስለምትመልስልኝ፣

በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጣራለሁ።

8ጌታ ሆይ፤ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤

ከአንተም ሥራ ጋር የሚወዳደር ሥራ የለም።

9ጌታ ሆይ፤ አንተ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ፣

መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ፤

ለስምህም ክብር ይሰጣሉ፤

10አንተ ታላቅ ነህና፤ ታምራትም ትሠራለህ፤

አንተ ብቻህን አምላክ ነህ።

11እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤

በእውነትህም እሄዳለሁ፤

ስምህን እፈራ ዘንድ፣

ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ።

12ጌታ አምላኬ ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤

ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ፤

13ለእኔ ያሳየሃት ምሕረት ታላቅ ናትና፤

ነፍሴንም ከሲኦል86፥13 አንዳንዶች መቃብር ይላሉ። ጥልቀት አውጥተሃል።

14አምላክ ሆይ፤ እብሪተኞች ተነሥተውብኛል፤

የዐመፀኞችም ጉባኤ ነፍሴን ይሿታል፤

አንተንም ከምንም አልቈጠሩም።

15ጌታ ሆይ፤ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤

ለቍጣ የዘገየህ፣ ምሕረትህና ታማኝነትህ የበዛ።

16ወደ እኔ ተመልከት፤ ማረኝም፤

ለባሪያህ ኀይልህን ስጥ፤

የሴት ባሪያህንም86፥16 ታማኝ ወንድ ልጅህን የሚሉ አሉ። ልጅ አድን።

17የሚጠሉኝ አይተው ያፍሩ ዘንድ፣

የበጎነትህን ምልክት አሳየኝ፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ረድተኸኛልና፤ አጽናንተኸኛልም።