መዝሙር 74 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 74:1-23

መዝሙር 74

ስለ መቅደሱ መፍረስ የቀረበ ጸሎት

የአሳፍ ትምህርት።

1አምላክ ሆይ፤ ለዘላለም የጣልኸን ለምንድን ነው?

በማሰማሪያህ ባሉ በጎችህስ ላይ ቍጣህ ለምን ነደደ?

2ጥንት ገንዘብህ ያደረግሃትን ጉባኤ፣

የዋጀሃትን የርስትህን ነገድ፣

መኖሪያህ ያደረግሃትን የጽዮን ተራራ ዐስብ።

3ርምጃህን ለዘላለሙ ባድማ ወደ ሆነው አቅና፤

ጠላት በመቅደስህ ውስጥ ያለውን ሁሉ አበላሽቷል።

4ጠላቶችህ በመገናኛ ስፍራህ መካከል ደነፉ፤

አርማቸውንም ምልክት አድርገው በዚያ አቆሙ።

5በጫካ መካከል ዛፎችን ለመቍረጥ፣

መጥረቢያ የሚያነሣ ሰው መሰሉ።

6በእደ ጥበብ ያጌጠውን ሥራ ሁሉ፣

በመጥረቢያና በመዶሻ ሰባበሩት።

7መቅደስህን አቃጥለው አወደሙት፤

የስምህንም ማደሪያ አረከሱ።

8በልባቸውም፣ “ፈጽሞ እንጨቍናቸዋለን” አሉ፤

እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ የተመለከበትን ስፍራ ሁሉ አቃጠሉ።

9የምናየው ምልክት የለም፤

ከእንግዲህ የሚነሣ አንድም ነቢይ የለም፤

ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል የሚያውቅ በእኛ ዘንድ የለም።

10አምላክ ሆይ፤ ጠላት የሚያሾፈው እስከ መቼ ነው?

ባላንጣስ ለዘላለም በስምህ ያላግጣልን?

11እጅህን ለምን ትሰበስባለህ?

ቀኝ እጅህን ለምን በብብትህ ሥር ታቈያለህ?

12አምላክ ሆይ፤ አንተ ከጥንት ጀምሮ ንጉሤ ነህ፤

በምድር ላይ ማዳንን አደረግህ።

13ባሕርን በኀይልህ የከፈልህ አንተ ነህ፤

የባሕሩንም አውሬ ራሶች በውሃ ውስጥ ቀጠቀጥህ።

14የሌዋታንን ራሶች አደቀቅህ፤

ለምድረ በዳ ፍጥረታትም ምግብ አድርገህ የሰጠሃቸው፣

15ምንጮችንና ፈሳሾችን ያፈለቅህ አንተ ነህ፤

ሳያቋርጡ የሚፈስሱትንም ወንዞች አደረቅህ።

16ቀኑ የአንተ ነው፤ ሌሊቱም የአንተ ነው፤

ጨረቃንና ፀሓይን አንተ አጸናሃቸው።

17የምድርን ዳርቻ ሁሉ የወሰንህ አንተ ነህ፤

በጋውንም ክረምቱንም አንተ ሠራህ።

18እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላት እንዴት እንደሚያሾፍ፣

ከንቱ ሕዝብም ስምህን እንዴት እንዳቃለለ ዐስብ።

19የርግብህን ነፍስ አሳልፈህ ለዱር አራዊት አትስጥ፤

የችግረኞች ሕዝብህን ሕይወት ለዘላለሙ አትርሳ።

20ኪዳንህን ዐስብ፤

የዐመፅ መናኸሪያ በምድሪቱ ጨለማ ስፍራዎች ሞልተዋልና።

21የተጨቈኑት ዐፍረው አይመለሱ፤

ድኾችና ችግረኞች ስምህን ያመስግኑ።

22አምላክ ሆይ፤ ተነሥ፤ ለዐላማህ ተሟገት፤

ከንቱ ሰው ቀኑን ሙሉ እንደሚያላግጥብህ ዐስብ።

23የባላጋራዎችህን ድንፋታ፣

ዘወትር የሚነሣውን የጠላቶችህን ፉከራ አትርሳ።