መዝሙር 67 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 67:1-7

መዝሙር 67

የመከር ጊዜ መዝሙር

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር፤ ማሕሌት።

1እግዚአብሔር ይማረን፤ ይባርከን፤

ፊቱንም በላያችን ያብራ፤ ሴላ

2መንገድህ በምድር ላይ፣

ማዳንህም በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይታወቅ ዘንድ።

3እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤

ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።

4ለሕዝቦች በቅን ስለምትፈርድላቸው፣

ሰዎችንም በምድር ላይ ስለምትመራ፣

ሕዝቦች ደስ ይበላቸው፤ በእልልታም ይዘምሩ። ሴላ

5እግዚአብሔር ሆይ፤ ሰዎች ያመስግኑህ፤

ሰዎች ሁሉ ምስጋና ያቅርቡልህ።

6ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤

እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።

7እግዚአብሔር ይባርከናል፤

የምድርም ዳርቻዎች ሁሉ እርሱን ይፈሩታል።