መዝሙር 56 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 56:1-13

መዝሙር 56

በእግዚአብሔር መደገፍ

ለመዘምራን አለቃ፤ “ርግቢቱ ሩቅ ባለው ወርካ ላይ” በተባለው ቅኝት፤ ፍልስጥኤማውያን በጌት በያዙት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ56 ርእሱ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰዎች መረገጫ ሆኛለሁና ማረኝ፤

ቀኑንም ሙሉ በውጊያ አስጨንቀውኛል።

2ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ በላዬ ቆሙ፤

በትዕቢት የሚዋጉኝ ብዙዎች ናቸውና።

3ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣

እምነቴን በአንተ ላይ አደርጋለሁ።

4ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣

በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤

ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?

5ቀኑን ሙሉ ቃሌን ያጣምሙታል፤

ዘወትርም ሊጐዱኝ ያሤራሉ።

6ይዶልታሉ፤ ያደባሉ፤

ርምጃዬን ይከታተላሉ፤

ነፍሴንም ለማጥፋት ይሻሉ።

7እግዚአብሔር ሆይ፤ ከቶ እንዳያመልጡ፣

ሕዝቦቹን በቍጣህ ጣላቸው።

8ሰቈቃዬን መዝግብ፤

እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤56፥8 እንባዬን በወይን አቍማዳህ ውስጥ ጨምር ወይም እንባዬን በመጽሐፍህ መዝገብ

ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?

9ወደ አንተ በተጣራሁ ቀን፣

ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤

በዚህም፣ አምላክ ከጐኔ መቆሙን ዐውቃለሁ።

10ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣

ቃሉን በማመሰግነው በእግዚአብሔር

11በአምላክ ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤

ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?

12እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተ ስእለት አለብኝ፤

የማቀርብልህም የምስጋና መሥዋዕት ነው፤

13በሕያዋን ብርሃን፣56፥13 ወይም በሕይወት ብርሃን

በእግዚአብሔር ፊት እመላለስ ዘንድ፣

ነፍሴን ከሞት፣56፥13 ወይም እኔን ከሞት

እግሬንም ከመሰናክል አድነሃልና።