መዝሙር 46 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 46:1-11

መዝሙር 4646 ርእስ ምናልባት የሙዚቃውን ሁኔታ ሊያሳይ ይችላል።

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር፤ በደናግል የዜማ ስልት የሚዘመር መዝሙር።

1አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣

በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።

2ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፣

ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ አንፈራም።

3ውሆች ቢያስገመግሙ፣ ዐረፋ ቢደፍቁም፣ ተራሮችም ከውሆቹ ሙላት የተነሣ

ቢንቀጠቀጡም አንደናገጥም። ሴላ

4የእግዚአብሔርን ከተማ፣

የልዑልን የተቀደሰ ማደሪያ ደስ የሚያሰኙ የወንዝ ፈሳሾች አሉ።

5እግዚአብሔር በመካከሏ ነው፤ አትናወጥም፤

አምላክ በማለዳ ይረዳታል።

6ሕዝቦች በዐመፅ ተነሡ፤ መንግሥታትም ወደቁ፤

ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰማ፤ ምድርም ቀለጠች።

7የሰራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤

የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ

8ኑና የእግዚአብሔርን ሥራ፣

ምድርንም እንዴት ባድማ እንዳደረጋት እዩ።

9ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤

ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤

ጋሻንም46፥9 ወይም ሠረገላንም በእሳት ያቃጥላል።

10“ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤

በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤

በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”

11የሰራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤

የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ