መዝሙር 44 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 44:1-26

መዝሙር 44

ብሔራዊ ሰቈቃ

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች ትምህርት44 የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

1አምላክ ሆይ፤ በጆሯችን ሰምተናል፤

አባቶቻችን በቀድሞ ዘመን፣

እነርሱ በነበሩበት ዘመን፣

ያደረግኸውን ነግረውናል።

2ሕዝቦችን በእጅህ አሳድደህ አወጣሃቸው፤

አባቶቻችንን ግን ተከልሃቸው፤

ሕዝቦችን አደቀቅህ፤

አባቶቻችንን ግን ነጻ አወጣሃቸው።

3ምድሪቱን የወረሱት በሰይፋቸው አልነበረም፤

ድልንም የተጐናጸፉት በክንዳቸው አይደለም፤

አንተ ወድደሃቸዋልና ቀኝ እጅህ፣

ክንድህና የፊትህ ብርሃን ይህን አደረገ።

4እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ንጉሤ ነህ፤44፥4 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም የሱርስቱ ቅጅ ንጉሤ ነህ፤ አምላኬም ነህ ይላሉ፤ ዕብራይስጡ ደግሞ፣ ንጉሤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይላል።

ያዕቆብም ድል እንዲያደርግ የወሰንህ አንተ ነህ።

5በአንተ ጠላቶቻችን በመጡበት እንዲመለሱ እናደርጋለን፤

በስምህም ባላጋራዎቻችንን ከእግራችን በታች እንረግጣለን።

6በቀስቴ አልተማመንም፤

ሰይፌም አያስጥለኝም።

7አንተ ግን በጠላቶቻችን ላይ ድልን ትሰጠናለህ፤

ባላንጣዎቻችንንም ታሳፍራለህ።

8ዘወትር በእግዚአብሔር እንመካለን፤

ስምህንም ለዘላለም እንወድሳለን። ሴላ

9አሁን ግን እነሆ ትተኸናል፤ አሳፍረኸናልም፤

ከሰራዊታችንም ጋር አትወጣም።

10ከጠላት ፊት እንድናፈገፍግ አደረግኸን፤

ባላንጣዎቻችንም ዘረፉን።

11እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤

በሕዝቦችም መካከል በተንኸን።

12ሕዝብህን በርካሽ ዋጋ ሸጥኸው፤

ከሽያጩም ያገኘኸው ትርፍ የለም።

13ለጎረቤቶቻችን ስድብ፣

በዙሪያችን ላሉትም መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን።

14በሕዝቦች ዘንድ መተረቻ፣

በሰዎች መካከል በንቀት ራስ መነቅነቂያ አደረግኸን።

15ውርደቴ ቀኑን ሙሉ በፊቴ ነው፤

ፊቴም ዕፍረትን ተከናንቧል።

16ይህም ከሚዘልፍና ከሚያላግጥ ሰው ድምፅ የተነሣ፣

ከጠላትና ከተበቃይ ሁኔታ የተነሣ ነው።

17አንተን ሳንረሳ፣

ለኪዳንህም ታማኝነታችንን ሳናጓድል፣

ይህ ሁሉ ደረሰብን።

18ልባችን ወደ ኋላ አላለም፤

እግራችንም ከመንገድህ አልወጣም።

19አንተ ግን ተኵላዎች በሚውሉበት ቦታ ሰባብረህ ጣልኸን፤

በሞት ጥላም ሸፈንኸን።

20የአምላካችንን ስም ረስተን፣

እጃችንንም ወደ ባዕድ አምላክ ዘርግተን ቢሆን ኖሮ፣

21እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሳነዋልን?

እርሱ ልብ የሰወረውን የሚረዳ ነውና።

22ይሁን እንጂ ቀኑን ሙሉ ስለ አንተ ሞትን እንጋፈጣለን፤

እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጥረናል።

23ጌታ ሆይ፤ ንቃ! ለምንስ ትተኛለህ?

ተነሥ፤ ለዘላለምም አትጣለን።

24ፊትህን ለምን ትሰውራለህ?

መከራችንንና መጠቃታችንን ለምን ትረሳለህ?

25ነፍሳችን ዐፈር ውስጥ ሰጥማለች፤

ሆዳችንም ከምድር ጋር ተጣብቋል።

26ተነሥና እርዳን!

ስለ ምሕረትህ ስትል ተቤዠን።