መዝሙር 41 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 41:1-13

መዝሙር 41

የሕመምተኛና የብቸኛ ሰው ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1ለድኾች የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው፤

እርሱንም እግዚአብሔር በክፉ ቀን ይታደገዋል።

2እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፤ በሕይወትም ያኖረዋል፤

በምድርም ላይ ይባርከዋል፤

ለጠላቶቹም ምኞት አሳልፎ አይሰጠውም።

3ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይ እግዚአብሔር ይንከባከበዋል፤

በበሽታውም ጊዜ መኝታውን ያነጥፍለታል።

4እኔም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረት አድርግልኝ፤

አንተን በድያለሁና ነፍሴን ፈውሳት” አልሁ።

5ጠላቶቼ በክፋት በመናገር፣ “የሚሞተው መቼ ነው? ስሙስ

የሚደመሰሰው ምን ቀን ነው?” ይላሉ።

6ሊጠይቀኝ የሚመጣ ቢኖር፣

በልቡ ስድብ እያጠራቀመ፣ ከዐንገት በላይ ይናገራል፤

ወጥቶም ወሬ ይነዛል።

7ጠላቶቼ ሁሉ ግንባር ፈጥረው ይንሾካሾኩብኛል፤

እንዲህ እያሉም፣

የከፋ ነገር በላዬ ያውጠነጥናሉ፤

8“ክፉ ደዌ ይዞታል፤

ከእንግዲህም ከተኛበት አይነሣም።”

9እንጀራዬን ተካፍሎኝ የበላ፣

የምተማመንበትም የቅርብ ወዳጄ፣

በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ።

10እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ምሕረት አድርግልኝ፤

የእጃቸውን እንድከፍላቸው አስነሣኝ።

11ጠላቴ በላዬ ድል አላገኘምና፣

እንደ ወደድኸኝ በዚህ ዐወቅሁ።

12ስለ ጭንቀቴ ደግፈህ ይዘኸኛል፤

በፊትህም ለዘላለም ታኖረኛለህ።

13የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር

ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን፤

አሜን፤ አሜን።