መዝሙር 35 – New Amharic Standard Version (NASV)

New Amharic Standard Version

መዝሙር 35:1-28

መዝሙር 35

የተጨቈነ ሰው ጸሎት

የዳዊት መዝሙር

1እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚታገሉኝን ታገላቸው፤

የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው።

2ትልቁንና ትንሹን ጋሻ ያዝ፤

እኔንም ለመርዳት ተነሥ።

3በሚያሳድዱኝ ላይ፣

ጦርና ጭሬ ምዘዝ፤35፥3 ወይም … መንገድ ዝጋ

ነፍሴንም፣

“የማድንሽ እኔ ነኝ” በላት።

4ሕይወቴን የሚፈልጓት፣

ይቅለሉ፣ ይዋረዱ፤

እኔን ለማጥፋት የሚያሤሩ፣

ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።

5በነፋስ ፊት እንዳለ እብቅ ይሁኑ፤

የእግዚአብሔር መልአክ ያሳዳቸው።

6መንገዳቸው ጨለማና ድጥ ይሁን፤

የእግዚአብሔር መልአክ ያባራቸው።

7ያለ ምክንያት ወጥመዳቸውን በስውር አስቀምጠውብኛልና፤

ያለ ምክንያት ለነፍሴ ጒድጓድ ቈፍረውላታል።

8ያልታሰበ ጥፋት ይምጣባቸው፤

የሰወሩት ወጥመድ ይያዛቸው፤

ይጠፉም ዘንድ ወደ ጒድጓዱ ይውደቁ።

9ነፍሴም በእግዚአብሔር ደስ ይላታል፤

በማዳኑም ሐሤት ታደርጋለች።

10የሠራ አካላቴ እንዲህ ይልሃል፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ማን አለ?

ድኻውን ከእርሱ ከሚበረቱ፣

ችግረኛውንና ምስኪኑን ከቀማኞች ታድናለህ”።

11ጨካኝ ምስክሮች ተነሡ፤

ስለማላውቀውም ነገር ጠየቁኝ።

12በበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤

ነፍሴንም ብቸኛ አደረጓት።

13እኔ ግን እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፤

ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፤

ጸሎቴም መልስ አጥቶ ወደ ጒያዬ ተመለሰ።

14ለወዳጄ ወይም ለወንድሜ እንደማደርግ፣

እየተንቈራጠጥሁ አለቀስሁ፤

ለእናቴም እንደማለቅስ፣

በሐዘን ዐንገቴን ደፋሁ።

15እነርሱ ግን እኔ ስሰናከል በእልልታ ተሰበሰቡ፤

ግፈኞች በድንገት ተሰበሰቡብኝ፤

ያለ ዕረፍትም ቦጫጨቁኝ።

16እንደ ምናምንቴዎች አፌዙብኝ፤35፥16 ሰብዓ ሊቃናት እንዲሁ ሲሆን በዕብራይስጥ ግን ምናምንቴ ፌዘኞች ማለት ሊሆን ይችላል።

ጥርሳቸውንም አፋጩብኝ።

17ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ ዝም ብለህ ታያለህ?

ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው፣

ብርቅ ሕይወቴን ከአንበሶች ታደጋት።

18በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ፤

ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበትም አወድስሃለሁ።

19ከምድር ተነሥተው ጠላቶቼ የሆኑት፣

በላዬ ደስ አይበላቸው፤

እንዲያው የሚጠሉኝ፣

በዐይናቸው አይጣቀሱብኝ።

20የሰላም ንግግር ከአፋቸው አይወጣም፤

ዳሩ ግን በምድሪቱ በጸጥታ በሚኖሩት ላይ፣

ነገር ይሸርባሉ።

21አፋቸውን አስፍተው ከፈቱብኝ፤

“ዕሠይ! ዕሠይ! በዐይናችን አየነው” አሉ።

22እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን አይተሃልና ዝም አትበል፤

ጌታ ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ።

23አምላኬ፣ ጌታዬ፤ ለእኔ ለመሟገት ተነሥ!

ልትከራከርልኝም ተንቀሳቀስ።

24እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ በጽድቅህ ፍረድልኝ፤

በእኔም ላይ ደስ አይበላቸው።

25በልባቸው፣ “ዕሠይ! ያሰብነው ተሳካ!

ዋጥ አደረግነውም” አይበሉ።

26በጭንቀቴ ደስ የሚላቸው፣

ይፈሩ፤ ግራም ይጋቡ፤

በእኔ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ፣

ዕፍረትንና ውርደትን ይከናነቡ።

27ፍትሕ ማግኘቴን የሚወዱ፣

እልል ይበሉ፤ ሐሤትም ያድርጉ፤

ዘወትርም፣ “የባርያው ሰላም ደስ የሚለው፣

እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ።

28አንደበቴ ጽድቅህን፣

ምስጋናህንም ቀኑን ሙሉ ይናገራል።