መዝሙር 32 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 32:1-11

መዝሙር 32

ግልጥ ኑዛዜ

የዳዊት ትምህርት።

1መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣

ኀጢአቱም የተሸፈነለት፣

እንዴት ቡሩክ ነው!

2እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣

በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው፣

እርሱ ቡሩክ ነው።

3ቀኑን ሙሉ ከመቃተቴ የተነሣ፣

ዝም ባልሁ ጊዜ፣

ዐጥንቶቼ ተበላሹ፤

4በቀንና በሌሊት፣

እጅህ ከብዳብኛለችና፤

ኀይሌም የበጋ ትኵሳት እንደ ላሰው ነገር፣

ከውስጤ ተሟጠጠ። ሴላ

5ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤

በደሌንም አልሸሸግሁም፤

ደግሞም “መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ” አልሁ፤

አንተም የኀጢአቴን በደል፣

ይቅር አልህ። ሴላ

6ስለዚህ ጻድቅ ሁሉ፣

በጭንቅ ጊዜ ወደ አንተ ይጸልይ፤

ኀይለኛ ጐርፍ አካባቢውን ቢያጥለቀልቅም፣

እርሱ አጠገብ አይደርስም።

7አንተ መሸሸጊያዬ ነህ፤

ከመከራ ትጠብቀኛለህ፤

በድል ዝማሬም ትከብበኛለህ። ሴላ

8አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤

እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።

9በልባብና በልጓም ካልተገሩ በቀር፣

ወደ አንተ እንደማይቀርቡት፣

ማስተዋል እንደሌላቸው፣

እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ።

10የክፉዎች ዋይታ ብዙ ነው፤

በእግዚአብሔር የሚታመን ግን፣

ምሕረት ይከብበዋል።

11ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤

ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ እልል በሉ።