መዝሙር 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 3:1-8

መዝሙር 3

የመከራ ተቀባዩ የጧት ጸሎት

ዳዊት ከልጁ ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ የዘመረው መዝሙር።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ ምንኛ በዙ!

ስንቱስ በእኔ ላይ ተነሣ!

2ብዙዎች ነፍሴን፣ “እግዚአብሔር

አይታደግሽም” አሏት። ሴላ3፥2 በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚገኝ ሲሆን፣ የቃሉ ትርጕም በትክክል አይታወቅም፤ የሙዚቃ ምልክት ሳይሆን አይቀርም

3እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ዙሪያዬን

የምትከልል ጋሻ ነህ፤

ክብሬንና ራሴንም ቀና ቀና

የምታደርግ አንተ ነህ።3፥3 ወይም እግዚአብሔር… ወደ ላይ የምታነሣ ክብሬ ሆይ

4ወደ እግዚአብሔር ድምፄን ከፍ አድርጌ እጮሃለሁ፤

እርሱም ከተቀደሰ ተራራው ይመልስልኛል። ሴላ

5እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁ፤

እግዚአብሔር ደግፎ ይዞኛልና እነቃለሁ።

6በየአቅጣጫው የከበበኝን፣

አእላፍ ሕዝብ አልፈራም።

7እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ!

አምላኬ ሆይ፤ ታደገኝ፤

የጠላቶቼን ሁሉ መንጋጋ ትመታለህ፤

የክፉዎችንም ጥርስ ትሰባብራለህ።

8ማዳን የእግዚአብሔር ነው፤

በረከትህ በሕዝብህ ላይ ይሁን። ሴላ