መዝሙር 17 – New Amharic Standard Version (NASV)

New Amharic Standard Version

መዝሙር 17:1-15

መዝሙር 17

የንጹሕ ሰው አቤቱታ

የዳዊት ጸሎት

1እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅንነት የቀረበውን አቤቱታዬን ስማ፤

ጩኸቴንም አድምጥ፤

ከአታላይ ከንፈር ያልወጣውን፣

ጸሎቴን አድምጥ።

2ጽድቄ ከአንተ ዘንድ ይምጣ፤

ዐይኖችህም ፍትሕን ይዩ።

3ልቤን መረመርኸው፣ በሌሊት ጠጋ

ብለህ ፈተንኸኝ፤

ፈተሽኸኝ አንዳች አላገኘህብኝም፤

አንደበቴም ዕላፊ አልሄደም።

4ከሰዎች ተግባር፣

በከንፈርህ ቃል፣

ከዐመፀኞች መንገድ፣

ራሴን ጠብቄአለሁ።

5አረማመዴ በመንገድህ ጸንቶአል፤

እግሮቼም አልተንሸራተቱም።

6አምላክ ሆይ፤ ስለምትመልስልኝ አንተን እጣራለሁ፤

ጆሮህን ወደ እኔ ጣል አድርገህ ጸሎቴን ስማ።

7ከጠላቶቻቸው መተገኛ ያደረጉህን፣

በቀኝ እጅህ የምትታደግ ሆይ፤

ጽኑ ፍቅርህን ድንቅ አድርገህ ግለጥ።

8እንደ ዐይንህ ብሌን ጠብቀኝ፤

በክንፎችህም ጥላ ሰውረኝ፤

9ከሚያስጨንቁኝ ከክፉዎች፣

ከሚከብቡኝ አደገኛ ባላንጣዎቼ ጋርደኝ።

10ደንዳና ልባቸውን ደፈኑት፤

በአፋቸውም ትዕቢት ይናገራሉ።

11አሳደው ደረሱብኝ፤ ከበቡኝም፤

መሬት ላይ ሊዘርሩኝም አፈጠጡብኝ።

12እነርሱ ለንጥቂያ እንደሚጓጓ አንበሳ፣

በስውርም እንደሚያደባ ደቦል አንበሳ ናቸው።

13እግዚአብሔር ሆይ፤ ተነሥተህ ግጠማቸውና ጣላቸው፤

በሰይፍህም ከክፉዎች ታደገኝ።

14እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ካሉት ሰዎች በክንድህ አድነኝ፤

ዕድል ፈንታቸው ይህችው ሕይወት ብቻ ከሆነች፣ ከዚህ ዓለም ሰዎች ታደገኝ።

ከመዝገብህ ሆዳቸውን ሞላህ፤

ልጆቻቸውም ተትረፍርፎላቸዋል፤

ለልጆቻቸውም ሀብት ያከማቻሉ።

15እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤

ስነቃም ክብርህን አይቼ እረካለሁ።