መዝሙር 16 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 16:1-11

መዝሙር 16

እግዚአብሔር ርስቴ

የዳዊት ቅኔ።

1አምላክ ሆይ፤ መጠጊያዬ ነህና፣

በከለላህ ሰውረኝ።

2እግዚአብሔርን፣ “አንተ ጌታዬ ነህ፤

ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም”

አልሁት።

3በምድር ያሉ ቅዱሳን፣

ሙሉ ደስታ የማገኝባቸው ክቡራን ናቸው።16፥3 ወይም በምድሪቱ ላሉ አረማውያን፣ ካህናትና ደስ ለተሰኙባቸው መኳንንት ሁሉ ይህን እላለሁ

4ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ፣

ሐዘናቸው ይበዛል፤

እኔ ግን የደም ቍርባናቸውን አላፈስስም፤

ስማቸውንም በአፌ አልጠራም፤

5እግዚአብሔር የርስት ድርሻዬና ጽዋዬ ነው፤

ዕጣዬም በእጅህ ናት።

6መካለያ ገመድ ባማረ ስፍራ ተጥሎልኛል፤

በርግጥም የተዋበች ርስት አግኝቻለሁ።

7የሚመክረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤

በሌሊት እንኳ ልቤ ቀናውን ያመላክተኛል።

8እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤

እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም።

9ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ ነፍሴም ሐሤት አደረገች፤

ሥጋዬም ያለ ሥጋት ዐርፎ ይቀመጣል፤

10በሲኦል16፥10 ወይም በመቃብር ውስጥ አትተወኝምና፤

ቅዱስህም16፥10 ወይም በአንተ የታመነውን መበስበስን እንዲያይ አታደርግም።

11የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤16፥11 ወይም ታሳውቀኛለህ

በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣

በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ።