መዝሙር 130 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 130:1-8

መዝሙር 130

ለርዳታ የቀረበ ጥሪ

መዝሙረ መዓርግ።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥልቅ ወደ አንተ እጮኻለሁ።

2ጌታ ሆይ፤ ድምፄን ስማ፤

ጆሮዎችህ የልመናዬን ቃል፣

የሚያዳምጡ ይሁኑ።

3እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣

ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?

4ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤

ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።

5እግዚአብሔርን ደጅ እጠናለሁ፤ ነፍሴም በትዕግሥት ትጠብቀዋለች፤

በቃሉም ተስፋ አደርጋለሁ።

6ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣

አዎን፤ ዘብ ዐዳሪ ንጋትን ከሚጠባበቅ ይልቅ፣

ነፍሴ ጌታን ትጠባበቃለች።

7በእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፣

በእርሱም ዘንድ ማዳን አለና፣

እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ።

8እርሱም እስራኤልን፣

ከኀጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።