መዝሙር 116 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 116:1-19

መዝሙር 116

ምስጋና

1የልመናዬን ድምፅ ሰምቷልና፣

እግዚአብሔርን ወደድሁት።

2ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሏልና፣

በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ወደ እርሱ እጣራለሁ።

3የሞት ወጥመድ ያዘኝ፤

የሲኦልም116፥3 ዕብራይስጡ መቃብር ይላል። ጣር አገኘኝ፤

ጭንቅና ሐዘን አሸነፈኝ።

4እኔም የእግዚአብሔርን ስም ጠራሁ፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ታድናት ዘንድ እለምንሃለሁ” አልሁ።

5እግዚአብሔር ቸርና ጻድቅ ነው፤

አምላካችን መሓሪ ነው።

6እግዚአብሔር ገሮችን ይጠብቃል፤

እጅግ ተቸግሬ ሳለሁ አዳነኝ።

7ነፍሴ ሆይ፤ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፤

እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና፤

8አንተ ነፍሴን ከሞት፣

ዐይኔን ከእንባ፣

እግሮቼን ከመሰናከል አድነሃልና።

9እኔም በሕያዋን ምድር፣

በእግዚአብሔር ፊት እመላለሳለሁ።

10“እጅግ ተጨንቄአለሁ” ባልሁበት ጊዜ እንኳ፣116፥10 ወይም ያኔ እንኳን

እምነቴን ጠብቄአለሁ።

11ግራ በተጋባሁ ጊዜ፣

“ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው” አልሁ።

12ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣

ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው?

13የመዳንን ጽዋ አነሣለሁ፤

የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።

14በሕዝቡ ሁሉ ፊት፣

ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ።

15የቅዱሳኑ ሞት፣

በእግዚአብሔር ፊት የተከበረ ነው።

16እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ በእውነት ባሪያህ ነኝ፤

እኔ የሴት ባሪያህ116፥16 ታማኝ አገልጋይህ ወይም ታማኝ ልጅህ ልጅ፣ ባሪያህ ነኝ፤

ከእስራቴም ፈታኸኝ።

17ለአንተ የምስጋና መሥዋዕት አቀርባለሁ፤

የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።

18በሕዝቡ ሁሉ ፊት፣

ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ፤

19ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ይህን በመካከልሽ፣

በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ አደርጋለሁ።

ሃሌ ሉያ።116፥19 አንዳንዶች እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ።