መዝሙር 109 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 109:1-31

መዝሙር 109

በጠላት ላይ የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1የምስጋናዬ ምንጭ የሆንህ አምላክ ሆይ፤ ዝም አትበል፤

2ክፉዎችና አታላዮች፣

አፋቸውን ከፍተውብኛልና፤

በውሸተኛ አንደበት ተናግረውብኛል።

3በጥላቻ ቃል ከብበውኛል፤

ያለ ምክንያትም ጥቃት አድርሰውብኛል።

4ስወድዳቸው ይወነጅሉኛል፤

እኔ ግን እጸልያለሁ።

5በበጎ ፈንታ ክፋትን፣

በወደድኋቸው ፈንታ ጥላቻን ይመልሱልኛል።

6ክፉ ሰው109፥6 ወይም ክፉው በላዩ ሹም፤

ከሳሽም109፥6 ወይም ሰይጣንን በቀኙ ይቁም።

7ፍርድ ፊት ሲቆም በደለኛ ሆኖ ይገኝ፤

ጸሎቱም ለፍርድ ትሁንበት።

8ዕድሜው ይጠር፤

ሹመቱንም ሌላ ይውሰደው።

9ልጆቹ ድኻ ዐደጎች ይሁኑ፤

ሚስቱም መበለት ትሁን።

10ልጆቹ ይንከራተቱ፤ ለማኞችም ይሁኑ፤

ከፈረሰው ቤታቸውም ይሰደዱ።

11ያለውን ሁሉ ዕዳ ጠያቂ ይውረሰው፤

የድካሙንም ዋጋ ባዕዳን ይቀሙት።

12ማንም ሰው ምሕረት አያድርግለት፤

ለድኻ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።

13ዘሩ ተለይቶ ይጥፋ፤

ስማቸውም በሚቀጥለው ትውልድ ይደምሰስ።

14የአባቶቹ በደል በእግዚአብሔር ፊት ይታሰብ፤

የእናቱም ኀጢአት አይደምሰስ።

15መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፉ ዘንድ፣

ኀጢአታቸው ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይኑር፤

16ችግረኛውንና ምስኪኑን፣ ልቡም የቈሰለውን፣

እስከ ሞት አሳደደ እንጂ፣

ምሕረት ያደርግ ዘንድ አላሰበምና።

17መራገምን ወደደ፤ ወደ እርሱም መጣች፤

በመባረክ ደስ አልተሰኘም፤

በረከትም ከእርሱ ራቀች።

18መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፤

እርሷም እንደ ውሃ ወደ ውስጥ ሰውነቱ፣

እንደ ዘይትም ወደ ዐጥንቱ ዘለቀች።

19ገላውን እንደሚሸፍንበት ልብስ፣

ዘወትር እንደሚታጠቀውም መቀነት ትሁነው።

20እግዚአብሔር ለሚወነጅሉኝ ሰዎች፣

በነፍሴም ላይ ክፉ ለሚናገሩ የሚከፍላቸው ይኸው ይሁን።

21አንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤

ስለ ስምህ በበጎ ተመልከተኝ፤

ምሕረትህም መልካም ናትና አድነኝ።

22እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝና፤

ልቤም በውስጤ ቈስሏልና።

23እንደ ምሽት ጥላ ከእይታ ተሰውሬአለሁ፤

እንደ አንበጣም ረግፌአለሁ።

24ከጾም የተነሣ ጕልበቴ ዛለ፤

ሰውነቴም ከስቶ ዐመድ ለበሰ።

25ለመሣለቂያ ሆንሁላቸው፤

ሲያዩኝም ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።

26እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ርዳኝ፤

እንደ ምሕረትህም አድነኝ።

27እግዚአብሔር ሆይ፤ እጅህ ይህን እንዳደረገች፣

አንተም ይህን እንደ ፈጸምህ ይወቁ።

28እነርሱ ይራገማሉ፤ አንተ ግን ትባርካለህ፤

በሚነሡበት ጊዜ ይዋረዳሉ፤

ባሪያህ ግን ሐሤት ያደርጋል።

29የሚወነጅሉኝ ውርደትን ይከናነቡ፤

ዕፍረትንም እንደ ሸማ ይልበሱ።

30እግዚአብሔርን በአንደበቴ እጅግ አመሰግናለሁ፤

በታላቅ ሕዝብም መካከል አወድሰዋለሁ።

31በነፍሱ ላይ ከሚፈርዱት ያድነው ዘንድ፣

እርሱ በችግረኛው ቀኝ በኩል ይቆማልና።