መዝሙር 106 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 106:1-48

መዝሙር 106

ብሔራዊ ኑዛዜ

106፥147-48 ተጓ ምብ – 1ዜና 16፥34-36

1ሃሌ ሉያ።106፥1 እግዚአብሔር ይመስገን ማለት ሲሆን፣ በ48 ላይም በድጋሚ ተጠቅሷል።

ቸር ነውና፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤

ምሕረቱም ለዘላለም ነውና።

2ስለ እግዚአብሔር ታላቅ ሥራ ማን ሊናገር ይችላል?

ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ተናግሮ ይጨርሳል?

3ፍትሕ እንዳይዛነፍ የሚጠብቁ፣

ጽድቅን ሁልጊዜ የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው።

4እግዚአብሔር ሆይ፤ ለሕዝብህ ሞገስ ስታድል አስበኝ፤

በምታድናቸውም ጊዜ ርዳኝ፤

5ይኸውም የምርጦችህን ብልጽግና አይ ዘንድ፣

በሕዝብህ ደስታ ደስ ይለኝ ዘንድ፣

ከርስትህም ክብር የተነሣ እጓደድ ዘንድ ነው።

6እኛም እንደ አባቶቻችን ኀጢአት ሠራን፤

በደልን፤ ክፉም አደረግን።

7አባቶቻችን በግብፅ ሳሉ፣

ታምራትህን አላስተዋሉም፤

የምሕረትህን ብዛት አላሰቡም፤

በባሕሩ አጠገብ፣ ገና ቀይ ባሕር106፥7 በዕብራይስጥ ያም ሱፍ የሚባል ሲሆን፣ የደንገል ባሕር ማለት ነው፤ በ9 እና 22 ላይም ይገኛል። አጠገብ ዐመፁብህ።

8እርሱ ግን የኀይሉን ታላቅነት ለማሳወቅ፣

ስለ ስሙ አዳናቸው።

9ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ እርሱም ደረቀ፤

በምድረ በዳ እንደሚታለፍ በጥልቅ ውሃ መካከል መራቸው።

10ከባለጋራቸው እጅ አዳናቸው፤

ከጠላትም እጅ ታደጋቸው።

11ባላንጦቻቸውን ውሃ ዋጣቸው፤

ከእነርሱም አንድ አልተረፈም።

12ከዚህ በኋላ የተስፋ ቃሉን አመኑ፤

በዝማሬም አመሰገኑት።

13ነገር ግን ያደረገውን ወዲያውኑ ረሱ፤

በምክሩም ለመሄድ አልታገሡም።

14በምድረ በዳ እጅግ መመኘት አበዙ፤

በበረሓም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።

15እርሱም የለመኑትን ሰጣቸው፤

ዳሩ ግን የሚያኰሰምን ሕመም ሰደደባቸው።

16በሰፈር በሙሴ ላይ፣

ለእግዚአብሔር በተቀደሰውም በአሮን ላይ ቀኑ።

17ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤

የአቤሮንን ወገን ሰለቀጠች።

18እሳት በጉባኤያቸው መካከል ነደደ፤

ነበልባሉም ክፉዎችን ፈጅቶ አስወገደ።

19በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤

ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።

20ክብራቸው የሆነውንም ሣር በሚበላ፣

በበሬ ምስል ለወጡ።

21በግብፅ ታላቅ ነገር ያደረገውን፣

ያዳናቸውን አምላክ ረሱ፤

22እርሱ ግን በካም ምድር ድንቅ ሥራ፣

በቀይ ባሕርም አስደናቂ ነገር አደረገ።

23ስለዚህ በመቅሠፍቱ እንዳያጠፋቸው ይመለስ ዘንድ፣

እርሱ የመረጠው ሙሴ በመካከል ገብቶ፣

በፊቱ ባይቆም ኖሮ፣

እንደሚያጠፋቸው ተናግሮ ነበር።

24ከዚያም በኋላ መልካሚቱን ምድር ናቁ፤

የተስፋ ቃሉንም አላመኑም።

25በድንኳኖቻቸው ውስጥ አጕረመረሙ፤

የእግዚአብሔርንም ድምፅ አላዳመጡም።

26በምድረ በዳ ሊጥላቸው፣

እጁን አንሥቶ ማለ፤

27ዘራቸውንም በሕዝቦች መካከል ሊጥል፣

ወደ ተለያየ ምድርም እንደሚበትናቸው ማለ።

28ራሳቸውን ከብዔል ፌጎር ጋር አቈራኙ፤

ለሙታን የተሠዋውን መሥዋዕት በሉ፤

29በሥራቸውም እግዚአብሔርን አስቈጡት፤

ቸነፈርም በላያቸው መጣ።

30ፊንሐስም ተነሥቶ ጣልቃ ገባ፤

ቸነፈሩም ተገታ፤

31ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ፣

ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።

32ደግሞም በመሪባ ውሃ አጠገብ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤

ሙሴም ከእነርሱ የተነሣ ተቸገረ፤

33የእግዚአብሔርንም መንፈስ ስላስመረሩት፣

ሙሴ የማይገባ ቃል ከአንደበቱ አወጣ።106፥33 አንዳንዶች ራሱን ባለመቈጣጠርና በችኰላ ተናገረ

34እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት፣

ሕዝቦችን ከማጥፋት ወደ ኋላ አሉ፤

35እንዲያውም ከሕዝቦቹ ጋር ተደባለቁ፤

ልማዳቸውንም ቀሠሙ፤

36ጣዖቶቻቸውንም አመለኩ፤

ይህም ወጥመድ ሆነባቸው።

37ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን

ለአጋንንት ሠዉ።

38የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ደም፣

ለከነዓን ጣዖታት የሠዉአቸውን፣

ንጹሕ ደም አፈሰሱ፤

ምድሪቱም በደም ተበከለች።

39በተግባራቸው ረከሱ፤

በድርጊታቸውም አመንዝሮች ሆኑ።

40ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤

ርስቱንም ተጸየፈ።

41ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው፤

ጠላቶቻቸውም በላያቸው ሠለጠኑ።

42ጠላቶቻቸው ጨቈኗቸው፤

በሥልጣናቸውም ሥር አዋሏቸው።

43እርሱ ብዙ ጊዜ ታደጋቸው፤

እነርሱ ግን ዐመፃን የሙጥኝ አሉ፤

በኀጢአታቸውም ተዋረዱ።

44ሆኖም ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ፣

ጭንቀታቸውን ተመለከተ፤

45ለእነርሱም ሲል ቃል ኪዳኑን ዐሰበ፤

እንደ ምሕረቱም ብዛት ከቍጣው ተመለሰ።

46የማረኳቸው ሁሉ፣

እንዲራሩላቸው አደረገ።

47አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ አድነን፤

ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እናቀርብ ዘንድ፣

አንተን በመወደስ እንጓደድ ዘንድ፣

ከሕዝቦች መካከል ሰብስበህ አምጣን።

48የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር

ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤

ሕዝብም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

ሃሌ ሉያ።