መዝሙር 105 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 105:1-45

መዝሙር 105

የእስራኤል ድንቅ ታሪክ

105፥1-15 ተጓ ምብ – 1ዜና 16፥8-22

1እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤

ሥራውንም በሕዝቦች መካከል ግለጡ።

2ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤

ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ።

3በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤

እግዚአብሔርን የሚሹት ልባቸው ደስ ይበለው።

4እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤

ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ።

5ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣

ታምራቱንና ከአፉ የወጣውን ፍርድ አስቡ፤

6እናንተ የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች፣

ለራሱም የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አስታውሱ።

7እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤

ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው።

8ኪዳኑን ለዘላለም፣

ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስታውሳል።

9ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን፣

ለይስሐቅም በመሐላ የተሰጠውን ተስፋ አይረሳም።

10ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣

ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤

11እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣

የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።”

12በቍጥር አነስተኞች ሆነው ሳሉ፣

እጅግ ጥቂትና ባይተዋሮች ሳሉ፣

13ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ሲንከራተቱ፣

ከአንዱ መንግሥት ወደ ሌላው ሲቅበዘበዙ፣

14ማንም ግፍ እንዲፈጽምባቸው አልፈቀደም፤

ስለ እነርሱም ነገሥታትን እንዲህ ሲል ገሠጸ፤

15“የቀባኋቸውን አትንኩ፤

በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።”

16በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤

የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤

17በባርነት የተሸጠውን ሰው፣

ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ።

18እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤

በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።

19የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣

የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።

20ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤

የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው።

21የቤቱ ጌታ፣

የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፤

22ይኸውም ሹማምቱን በራሱ መንገድ ይመራ ዘንድ፣

ታላላቆቹንም ጥበብ ያስተምር ዘንድ ነበር።

23እስራኤል ወደ ግብፅ ገባ፤

ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ።

24እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤

ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤

25ሕዝቡን እንዲጠሉ፣

በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ።

26ባሪያውን ሙሴን፣

የመረጠውንም አሮንን ላከ።

27እነርሱም ታምራታዊ ምልክቶችን በመካከላቸው፣

ድንቅ ነገሮቹንም በካም ምድር አደረጉ።

28ጨለማን ልኮ ምድሪቱን ጽልመት አለበሰ፤

እነርሱም በቃሉ ላይ ማመፅን ተዉ።

29ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ፤

ዓሦቻቸውንም ፈጀ።

30ምድራቸውም፣ የነገሥታታቸው እልፍኝ ሳይቀር፣

ጓጕንቸር ተርመሰመሰባቸው።

31እርሱ በተናገረ ጊዜ የዝንብ መንጋ መጣ፤

ትንኞችም ምድራቸውን ወረሩ።

32ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፤

ምድራቸውም ሁሉ መብረቅ አወረደ።

33ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፤

የአገራቸውንም ዛፍ ከተከተ።

34እርሱ በተናገረ ጊዜ አንበጣ መጣ፤

ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ ከተፍ አለ፤

35የምድሪቱንም ዕፀዋት ሁሉ በላ፤

የመሬታቸውንም ፍሬ ሙጥጥ አደረገ፤

36ደግሞም በአገራቸው ያለውን በኵር ሁሉ፣

የኀይላቸውንም ሁሉ በኵራት መታ።

37የእስራኤልንም ሕዝብ ብርና ወርቅ ጭኖ እንዲወጣ አደረገ፤

ከነገዶቻቸውም አንድም አልተደናቀፈም።

38እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና፣

ወጥተው ሲሄዱ ግብፅ ደስ አላት።

39ደመናን እንደ መጋረጃ ዘረጋላቸው፤

እሳትም በሌሊት አበራላቸው።

40በለመኑትም ጊዜ፣ ድርጭት አመጣላቸው፤

የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው።

41ዐለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ተንዶለደለ፤

እንደ ወንዝም በበረሓ ፈሰሰ።

42ለባሪያው ለአብርሃም የሰጠውን፣

ቅዱስ የተስፋ ቃሉን አስቧልና።

43ሕዝቡን በደስታ፣

ምርጦቹንም በእልልታ አወጣቸው።

44የሌሎችን ሕዝቦች ምድር ሰጣቸው፤

የእነዚህንም የድካም ፍሬ ወረሱ፤

45ይህም ሥርዐቱን ይጠብቁ ዘንድ፣

ሕጉንም ይፈጽሙ ዘንድ ነው።

ሃሌ ሉያ።105፥45 እግዚአብሔር ይመስገን የሚሉ ትርጕሞች አሉ።